“ከመቃብር ጓሮ ላይ ቆመው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እስከ ሲኦልም እንወርዳለን ያሉትን አሸባሪ ቡድኖች ኢትዮጵያ ሳትፈርስ ወደ ሲኦል መሸኘት ይኖርብናል”

176

“ከመቃብር ጓሮ ላይ ቆመው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እስከ ሲኦልም እንወርዳለን ያሉትን አሸባሪ ቡድኖች ኢትዮጵያ ሳትፈርስ ወደ ሲኦል መሸኘት ይኖርብናል”

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባላት እና ደጋፊዎች በባሕር ዳር ከተማ የደም ልገሳ እያካሄዱ ነው፡፡

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) “ደማችን በደም ዋጋ ለወደደን የመከላከያ ሠራዊት፣ ሕዝባዊ ሠራዊት እና ለልዩ ኃይል አባላት ይሁን” በሚል መሪ መልዕክት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባላት እና ደጋፊዎች በባሕር ዳር ከተማ የደም ልገሳ እያካሄዱ ነው፡፡

አሸባሪው የትህነግ ቡድን በቃጣው ትንኮሳ የሀገርን ህልውና ለመታደግ ከመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሰባሰቡት የሕዝባዊ ሠራዊት እና ልዩ ኃይል አባላት ዛሬም እንደትናንቱ በጀግንነት ቆመዋል፡፡ ሕዝቡም እንደትናንቱ በስንቅ፣ በትጥቅ እና በሞራል የሀገር ደጀንነቱን እያረጋገጠ ይገኛል፡፡

ለሀገር ህልውና እና ለሕዝቦች ነፃነት ዘብ ለቆመው ኃይል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባላት እና ደጋፊዎች በባሕር ዳር ከተማ ደም እየለገሱ ነው፡፡ ጦርነት የማይሰለቸው አሸባሪው የትህነግ ቡድን ዛሬም ሀገር ለማፍረስ እየጣረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ደም ስትለግስ ያገኘናት ታደለች ደሳለኝ ህይዎቱን ለሚሰጥ አካል ደም መለገሴ ቀላል መስዋእትነት ነው ብላለች፡፡ በቀጣይም እስከ ግንባር ድረስ በመዝለቅ ዋጋ ለመክፈል እና የሚፈልግባትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነች ተናግራለች፡፡

የአብን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ.ር) አሸባሪው ትህነግ በሀገር ላይ የህልውና ስጋት ከመሆን አልፎ የኢትዮጵያን መኖር ከማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች ጋር የሚሠራ አሸባሪ ቡድን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለሀገር ዘብ በጋራ የሚቆሙበት ወቅት መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የአብን አባላት እና ደጋፊዎች የሚለግሱት ደም ለኢትዮጵያ ነፃነት ከሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫ ለተሰባሰቡት የነፃነት ኃይሎች ይውላል ብለዋል ዶክተር ደሳለኝ፡፡ “እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነንና የምንለግሰው ደም አሸባሪው ቡድን በኃይል እና በእጽ አደንዝዞ ወደ ጦርነት ለማገዳቸው የትግራይ ምርኮኞች እና ቁስለኞችም ይውላል” ነው ያሉት፡፡

አሸባሪው ትህነግ በጎሰመው የጦርነት ነጋሪት ውስጥ ህጻናት፣ ሴቶች እና አረጋዊያንም በግዳጅ እየተሳተፉ መሆኑን ዶክተር ደሳለኝ አንስተዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በታሪክ ፊት ከሚያስወቅሰው ዝምታው ሊወጣ እና ሊያወግዝ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ከሁሉም ብሔሮች ተውጣጥተው ወደ ግንባሮች ካመሩት የልዩ ኃይል እና ሕዝባዊ ሠራዊት አባላት ጎን በመሰለፍ ለነፃነታቸው ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውንም ዶክተር ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡

“ኢትዮጵያ የዚህ ትውልድ አደራ ናት” ያሉት እና ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው የአብን የፖለቲካ ዘርፍ ኅላፊ ክርስቲያን ታደለ ናቸው፡፡ ሁሉም በየመክሊቱ ሀገርን ከህልውና ስጋት ነፃ ለማድረግ የየድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡ አባቶቻችን በዓለም አደባባይ ነፃነቷ ያልተደፈረ፣ ክብሯ ያልተገፈፈ እና ሉዓላዊት ሀገር አውርሰውን ማለፋቸውን አቶ ክርስቲያን አስታውሰዋል፡፡

የዛሬው ትውልድ የተከፋፈለች እና የተቆራረሰች ሀገር የመቀበል ፍላጎትም ሆነ ሞራል አይኖረውም ነው ያሉት፡፡ ለዚህም አሸባሪውን ቡድን ማስወገድ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ሕይዎቱን ለመስጠት ላልሳሳ ኃይል የሚተካ ደም መስጠት ዝቅተኛው መስዋእትነት ነውም ብለዋል፡፡

ከመቃብር ጓሮ ላይ ቆመው “ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እስከ ሲኦልም እንወርዳለን” ያሉትን አሸባሪ ቡድኖች ኢትዮጵያ ሳትፈርስ ወደ ሲኦል መሸኘት ይኖርብናልና ሰላም ለማስከበር ሁሉም ዘብ ሊቆም ይገባል ሲሉም አቶ ክርስቲያን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሽብርተኛው ትህነግ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ላፉት ሦስት አስርት ዓመታት የሚታወቅ መሆኑን የፖለቲካ ዘርፍ ኅላፊው አንስተዋል፡፡ አሁን የፖለቲካ ልዩነት አጥር አበጅተን ለየብቻ የምንቆምበት ወቅት ባለመሆኑ ወጣቱ በየደረጃው ካለው የፀጥታ ኃይል ጋር እየተናበበ ግዳጁን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“ኢትዮጵያን በታሪካዊ ዉኃ ልኳ ለማስቀመጥ እና ለትዉልድ ለማስረከብ ዛሬም እንደ ትናንቱ እንዋደቃለን” የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍ እና የልማት ማኅበር
Next articleከባሌና ምዕራብ ወለጋ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለሚቀላቀሉ ወጣቶች ሽኝት ተደረገላቸው።