ʺየአማራ ሕዝብ ከተዘናጋ ለመጥፋት መርጧል ማለት ነው” በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የሕግ መምህር

352

ʺየአማራ ሕዝብ ከተዘናጋ ለመጥፋት መርጧል ማለት ነው” በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የሕግ መምህር

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ የአማራ ጠላት ወያኔ ለዓመታት የፈጸመው በደል አልበቃው ብሎ ዛሬም ለሌላ በደል ተነስቷል፡፡ ከአማራ ላይ የማወራርደው ሂሳብ አለኝ ያለው አሸባሪው ትህነግ አማራን ሊያጠቃ በሚያስችለው ግንባር ሁሉ ውጊያ ከፍቷል፡፡ ያሰበውን ያሳካ ዘንድም የሚችለውን አቅም ሁሉ እየተጠቀመ ነው፡፡

በወቅታዊ ጉዳይ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የሕግ መምህር ደሞዝ ካሴ አሸባሪው ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ አወራርዳለሁ ብሎ የተነሳውና በተግባር እያደረገው ያለው አዲስ አይደለም ብለዋል፡፡

ከመነሻው ጀምሮ ለአማራ ሕዝብ ያለው ጥላቻ የታወቀ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ያለው አዲስ ነገር የአማራ ሕዝብ ራሱን ከሕልውና ስጋት ለማውጣት እያደረገ ያለው ትግል ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ትህነግ ከ1960ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በመዋቅር የተደገፈ ጥቃት ሲያደርስ እንደነበር ያስታወሱት የሕግ መምህሩ በአማራና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተደቀነውን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ ገዢውን የፖለቲካ ፓርቲ ጨምሮ የአማራ ሕዝብ ይመለከተኛል የሚሉ ፖለቲከኞች ሁሉ በጠላታቸው ላይ መተባበርና አንድ መሆን ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም የትህነግ ጥላቻ በአማራ ሕዝብ ብቻ እንደማይቀር አውቀው ከአማራ ሕዝብ ጋር በጋራ መሰለፍ እንደሚገባቸው ነው ያመላከቱት፡፡

ወታደራዊ አቅም ያለው በወታደራዊ አቅሙ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ እንደ ሕዝብ አንድ ሆኖ መቆም ይገባል፡፡ የአማራ ሕዝብ መዘናጋት ውስጥ የሚገባ ከሆነ ግን እንደ ሕዝብ ለመጥፋት መርጧል ማለት ነው ብለዋል፡፡

አሸባሪው ትህነግ እየፈጸመ ባለው ጀምላ ጭፍጨፋ ሕዝብን የመጥፋት መርጫ መርጧል፣ የአማራ ሕዝብም የመጥፋትን ምርጫ አይመርጥም፣ ለዚህም ዳር እስከዳር በመዝመት አጥፊውን ቡድን ሊደመስስ ይገባል ብለዋል፡፡

ትህነግን ለማጥፋትና በሕልውና ላይ የመጣውን አደጋ ለመመከት መተባበር ካልተቻለ ለመጥፋት መዘጋጄት ነውም ብለዋል፡፡ መተባበርና የድርሻን ጠጠር መወርወር ለአማራ ሕዝብ የቀረበ ብቸኛው ምርጫ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

አሸባሪው ትህነግ የሰው ማዕበል በመፍጠር ከፊት ለፊት ሴቶችንና ሕጻናትን እያስጨረሰ ነው ያሉት ምሁሩ ድርጊቱ በዓለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ይህም ወንጀል ጊዜው ሲደርስ የትህነግን ሰዎች ያስጠይቃል ብለዋል፡፡

ነገር ግን አሉ ምሁሩ ሕጻናትን ነው የሚያሰልፍ በሚል ሰበብ የፌዴራል፣ የክልል መንግሥታትና ሕዝቡ መዘናጋት የለባቸውም ነው ያሉት።
ታጥቆ የመጣን ኃይል መመከት ድርድር ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አለመሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ሕጻናትንና ሴቶችን ሊያተርፍ የሚችል አካሄድ ካለ መከተል ካልሆነ ግን ታጥቆ ከመጣ ኃይል ራስን የመከላከልና ራስን የማትረፍ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ነው ያሉት፡፡

አሸባሪው ትህነግ ማዕከላዊ መንግሥቱን ተቆጣጥሮት በነበረው ሰዓት ባፈራቸው ወዳጆች አማካኝነት ውዥንብር እየፈጠረ ነው ያሉት ምሁሩ የወያኔን ፕሮፓጋንዳ መመከት የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራት አለባቸውም ነው ያሉት፡፡

በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የኢትዮጵያ ወዳጆች እውነትን የማሳዬትና ፕሮፓጋንዳውን የመመከት ሥራ መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ የሕውልና ስጋት ውስጥ እንዳለ ተረድቶ ራሱን ለማዳን በሁሉም መንገድ መንቀሳቀስ ይገበዋልም ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“እነሱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሉ እንጦርጦስ ለመግባት እንደወሰኑት ሁሉ፣ እኛ ደግሞ ኢትዮጵያን ከብተና ለመታደግ ስንል የማንከፍለው ዋጋ የለም” በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
Next article“አሸባሪው ትህነግ የኢትዮጵያ ሕዝብን በማጋጨት ዕድሜውን ለማራዘም ጥረት የሚያደርግ ስብስብ ነው” የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ