
“እነሱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሉ እንጦርጦስ ለመግባት እንደወሰኑት ሁሉ፣ እኛ ደግሞ ኢትዮጵያን ከብተና ለመታደግ ስንል የማንከፍለው ዋጋ የለም” በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያስተላለፈው መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል።
የሽብርተኛው ትህነግ አመራሮች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሉ እንጦርጦስ ለመግባት እንደወሰኑ ከነገሩን ሰነባብተዋል፡፡ ትህነጋዊያን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሉ የሚቆጥቡት ሰው፤ ጉልበት፤ ጊዜና ሃብት እንደሌላቸው ደጋግመው አስታውቀዋል፡፡ ይሄንን ሰይጣናዊ እምነታቸውን “ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንጦርጦስ መግባት ካለብን እንገባለን ” በማለት ለኢትዮጵያ ያላቸውን ጫፍ የወጣ ጥላቻ እስከምን ድረስ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ የአሸባሪው ትህነግ አመራሮች በቃላት የተናገሩትን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የገቡትን ቃል በተግባር መተግበር ጀምረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከማናቸውም ጊዜ በላይ ቆርጠው ተነስተዋል፤ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር እጅና ጓንት ሆነው ኢትዮጵያን እየወጓት ነው፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ባላቸው ቁርጠኛ ውሳኔ መነሻነት አብዛኛውን የትግራይ ሕዝብ ለጦርነት አሰልፈውታል፤ በዚህም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚችል የትግራይ ተዋላጅ ሁሉ በጦርነቱ እንዲሳተፍ፤ ያልቻለ በገንዘብ፤ በመረጃ እንዲሁም በጸሎትም ጭምር ቢሆን ለኢትዮጵያ መፍረስ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ መመሪያ ተላልፎለታል፡፡
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ትህነግ የትግራይን ሕዝብ ለጦርነት እንዳሰለፈ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይሄም ማለት በተግባር እንደታየው እድሜቸው ለአቅመ ውትድርና ያልደረሱ ወንድና ሴት ህጻናትን፤ እንዲሁም እድሜቸው የገፋ እናቶችን፤ አዛውንቶችን ያካተተ መሆኑን ዓለም እየተመለከተው ነው፡፡ አሸባሪው ትህነግ ይሄን ያክል የሰው ኃይል ያሰለፈው በተለያዩ ግንባሮች ነው፤ በተለይም በራያ፤ አበርገሌ፤ ጠለምት፤ ወልቃይት፤ አፋርና በተወሰነ ደረጃ ደግሞ በኤርትራ ድንበር አካባቢ፡፡
ይህ በሚሊዮን የሚገመት የታጠቀና ያልታጠቀ እንዲሁም ለአቅመ ጦርነት ያልደረሰ ኃይል ቢያንስ በ6 ግንባሮች ተከፍሎ የየድርሻ ስምሪት ተሰጥቶታል፡፡ ይሁንና የጠላትን አጠቃላይ ስምሪት ስናየው ኢትዮጵያ ካላት ሁለንተናዊ አቅም አንጻር ያን ያክል አስጊና ግዙፍ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህም በላይ አሸባሪው ትህነግ በቂ የሎጅስቲክ አቅርቦት የሌለው መሆኑንም መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡
ሌላውና ወሳኙ ጉዳይ አሸባሪው ኃይል ኢትዮጵያን ለማፍረስ ወስኖ እየተንቀሳቀሰ ያለው፤ ወንድና ሴት ህፃናትን፤ አዛውንት እናቶችንና አባወራዎችን ጭምር በማሰለፍ ብቻ ሳይሆን፤ ይሄ ሁሉ ለግንባር የተዘጋጀ የሰው ኃይል የትጥቅ አቅም የለውም፡፡ ትህነግ በተወሰነ መልኩ የቡድን መሳሪያዎች እንዳሉት የሚታወቅ ቢሆንም፤ ይሄንን ሁሉ የሰው ኃይል ግን የማስታጠቅ አቅም እንደሌለው በተግባር ታይቷል፡፡ የጥይትና የነዳጅ ዲፖዎች በእጁ የሌለው መሆኑ ደግሞ ተራዛሚ አቅም እንዳይኖረው ያደርገዋል፡፡ ለዚህም ማሳያው በግንባር የሚታየው እውነታ ግማሹ የትህነግ ተዋጊ በጀሌው መገኘቱ ነው፡፡ ሃሳባቸውም ጀሌዎቹ ተዋጊዎች ከሚሞተው ጓደኛቸው እያነሱ እንዲታጠቁና ከሆነላቸው የኢትዮጵያን ሠራዊት ገድለው እንዲታጠቁ ነው፡፡ ለዚህ ሲባል ደግሞ ተዋጊዎቹ ድፍረት እንዲሰማቸው ሀሽሽ እንዲወስዱ በማድረግ የሚፈጸም የጭካኔ ጥግ ነው፡፡
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የአሸባሪው ትህነግ የትግል ስልት የውሸት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ውዥንብር መፍጠር፤ ተዋጊዎቹን በአደንዛዥ እጽ አስክሮ ወደጦርነት በመማገድ ‹ይሄን ከተማ ተቆጣጠርኩ› የሚል ወሬ በመልቀቅ የተከታዮቹን ሞራል ለመጠበቅ ውሸትን የማታገያ መሳሪያ አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ ግዙፍ የሰው ኃይል (Human Wave) ወደጦር ግንባር በመልቀቅ በሚያገኛቸው መለስተኛ ድሎች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ‹ኃያል ነን› የሚል መልዕክት ለማስተላፍ ያለ የሌለ የሰው ኃይል ዋጋ እየከፈለ ይገኛል፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያንስ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?
አሁን ወሳኙ ጥያቄ አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይሄን ያክል ቆርጦ ከተነሳ፤ እኛ ኢትዮጵያዊያንስ ምን ማድረግ አለብን? የሚለው ነው፡፡ ለዚህ መልሱ አጭርና ግልጽ ነው፤ ይሄውም እኛ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያ ሀገራችን ከብተና ለመታደግ ስንል ከአሸባሪው ትህነግ በበለጠ ሁኔታ መጨከን አለብን፡፡ ኢትዮጵያዊያን አቅማችን ኢትዮጵያን ለመበተን በሰይጣናዊ ስሜት ከተነሳው አሸባሪው ትህነግ ጋር የሚወዳደር አይደለም፤ በአያሌው በተሻለ ቁመና ላይ የምንገኝ ከራስችን አልፈን ለሌሎች ሀገራት ክንድ የሚሆን እምቅ ወታደራዊ አቅም አለን፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ኃይል በአንድ ቀን ማሰለፍ እንችላለን፡፡ ከዚህም በላይ ዓላማችን ሀገርን ከብተና የመታደግ የተቀደሰ ዓላማ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ከትህነግ የበለጠ መሳሪያ፤ የሎጅስቲክ አቅርቦት፤ የሰው ኃይል አለን፡፡ የደጀን አቅማችንም ከሚገመተው በላይ እጅግ ጠንካራ ነው፡፡ ስለዚህ ካንሰሩን ትህነግ በአስተማማኝ ሁኔታ ነቅሎ ለመጣል ከኛ ከኢትዮጵያዊያን የሚጠበቀው ዋነኛ ቁምነገር እንደ እሬት መምረር ብቻ ነው፤ ሌላው ሁሉ በእጃችን ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያን ይሄንን ያክል ለሀገሩ ለኢትዮጵያ ሟች ሕዝብ፤ ፅኑ መከላከያ፤ የኢኮኖሚ አቅም፤ የትጥቅ አቅም፤ እያለን አይደለም አሸባሪው ትህነግን ማናቸውም ኃይል አያሸንፈንም፡፡ ዋናው ነገር በሀገር ለመጣ ጨካኝ ኃይል እንደአመጣጡ መመለስ ነው፡፡ ስለሆነም መላው የሀገራችን ሕዝቦች ጦርነት ውስጥ መሆናችንን ተገንዝበን መንግሥት በየጊዜው የሚሰጣቸውን አቅጣጫዎች በመከተል፤ ሀገራችንን ከብተና ለመታደግ ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል፡፡ ወጣቱ ዛሬ ነገ ሳይል የሀገር መከላከያ ሠራዊትን፣ ልዩ ኃይላችንን ይቀላቀል፤ ቀሪው ደግሞ በሚሊሻነት ይሳተፍ፡፡
በአጠቃላይ የሀገራችን ሕዝብ ልክ በፋሽስት ጣሊያን ወቅት ሀገሩን ለመታደግ እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም በክተት ሊዘምት ይገባል፤ ምክንያቱም የገጠመን ጠላት የወራሪው ጣሊያን ተቀጥላ ነውና፡፡ ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ፤ የእናት ሀገር ኢትዮጵያን ደመኛ ጠላት እስከወዲያኛው ለመደምሰስ አምርሮ ሊነሳ ይገባል፡፡ የሀገር በታኙ አሸባሪው ትህነግ ሰይጣናዊ እቅድ መክሸፍ የሚችለው በሕዝባዊ ማዕበል ዘመቻ ነው፡፡ ለዚህም እናት ሀገራችንን ከፍርሰት ለመታደግ ሀገራዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የአሸባሪው ትህነግ ሀገር የመበተን ሰይጣናዊ እቅድ ለማክሸፍ ዋነኛው መፍትሔ የኢትዮጵያዊያን እንደ እሬት መምር ነው!!
እነሱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ከገቡ እኛ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማዳን ሲኦል ድረስ እንዘምታለን!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m