
“የሕዳሴው ግድብ የውኃ ሙሌት ግብጽና ሱዳን ሲያሰራጩት የነበረውን ሐሰተኛ መረጃ ያጋለጠ ነው” የዓረብ ሀገራት ግንኙነት ተመራማሪ ዛይድ ዜዳን አል-ሀሪሪ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ)የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት መገባደዱን በተያዘው ሳምንት መግለጻቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያና የዓረብ ሀገራት ግንኙነት ተመራማሪ ዛይድ ዜዳን አል-ሀሪሪ የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት ግብጽና ሱዳን በሙሌቱ ምክንያት የውኃ እጥረት ያጋጥመናል ብለው ሲያሰራጩት የነበረውን የሐሰት መረጃ ያጋለጠ መሆኑን ገልጸዋል።
የግድቡ ውኃ ሙሌት በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉዳት እንደማያደርስ ማሳያም ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ሙሌቱ ሁለቱ ሀገራት የግድቡን ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ እንዳይሞላ ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት ፍሬ አልባ ያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።
የውኃ ሙሌቱ የተከናወነው እ.አ.አ 2015 ሦስቱ ሀገራት በሱዳን ካርቱም በፈረሙት የመርሆዎች ስምምነት አማካኝነት ነው ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ሙሌቱን ያደረገችው በጥንቃቄና የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላሉባቸው ስጋቶች ምላሽ በሰጠ መልኩ ነው፤ ዓለም ሙሌቱ የተሳካ እንደነበር ለማየት ችሏል” ሲሉ ነው አል-ሀሪሪ የገለጹት።
እስካሁን የተከናወኑ የግድቡ ሥራዎች ግብጽና ሱዳንን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ማንም ላይ ጉልህ ጉዳት ለማድረስ ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላት እንዲረዱት ያስችላቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት መጠናቀቅ በተጨማሪ ሁለት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ ተርባይኖች ማንቀሳቀስ የሚያስችል የውኃ መጠን መያዝ መቻሉን የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ገልጸው ነበር።
ሁለቱ ተርባይኖች በወራት ጊዜ ውስጥ ኃይል እንደሚያመነጩ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ተናግረዋል።
ተርባይኖቹ ኤሌክትሪክ እንዲያመነጩ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ሥራ ለኹሉም ኢትዮጵያዊ ትልቅ የሚባል ስኬት እንደሆነ ነው ዛይድ ዜዳን አል-ሀሪሪ የሚገልጹት።
በተጨማሪም ሙሌቱና የተርባይኖቹ ሥራ መጀመር ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለውን እምነት እንዲጨምር እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።
የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለግብጽና ለሱዳን እንዲሁም ለቀጣናው ጥቅም የሚሰጥ እንደሆነም አመልክተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት ግብጽና ሱዳን የአቋም ለውጥ አሳይተው ወደ ድርድር እንዲመጡ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም ነው አል-ሀሪሪ ግምታቸውን ያስቀመጡት።
በአጠቃላይ በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተመዘገቡ ስኬቶች ግብጽና ሱዳን እንዲሁም አጋሮቻቸው የኢትዮጵያን ፍላጎትና አቋም አስመልክተው የሚያሰራጩትን የተዛባና የተሳሳተ መረጃ እንዲያስተካክሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ አፈጻጸም ከ80 በመቶ በላይ መድረሱ ይታወቃል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m