ʺከእንግዲህ አይኖርም ነገር ማለሳለስ ፣ እነርሱም አያርፉም እኛም አንመለስ “

508
ʺከእንግዲህ አይኖርም ነገር ማለሳለስ፣
እነርሱም አያርፉም እኛም አንመለስ “
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አንተ ዓለም ቆሞ ያጨበጨበለት፣ በጀግንነቱ የተደነቀበት፣ ጠላት ከባሕር ማዶ ሆኖ የተሸበረለት፣ ኃያላን ነን ያሉት እጅ የነሱለት፤ ጠላት እንደ ቆሎ በእጁ የሚጨብጥ፣ እንደ ቋንጣ ከፍም ላይ የሚያርመጠምጥ፣ የጠላትን ጉሮሮ ለማነቅ የሚቋምጥ፣ በግራው እያረሰ፣ በቀኙ እየተኮሰ፣ በሰፊ አውድማ ነጭና ጥቁር እያፈሰ፣ ገፍቶ የመጣ ጠላትን ከድንበር ማዶ እየመለሰ፣ ለእናት ሀገር ደም እያፈሰሰ፣ አጥንት እየከሰከሰ የኖረ ሕዝብ ልጅ ነህ፡፡
ውሽንፈር ከማይገፋው፣ ጠላት ገፍቶ ከማያልፈው፣ ትዕግስቱ እንደ ውቅያኖስ ከሰፋው፣ ልቡ ከደነደነው፣ በግርማው ከሚጥል፣ በአፈሙዙ ከሚነጥል ጀግና ሕዝብ የወጣህ የጀግና ልጅ ጀግና ነሕ፡፡ የአንተን ልብ የሚበልጥ አይደለም፣ በእኩል የሚቀመጥ ጠላት አይገጥምህም፣ ጠላትን በልብህ ኩራት፣ በአሞትህ ሙላት፣ ከአባት በወረስከው የጦር ብልሃት፣ የአተኳኮስ ሥርዓት ኹሉ ትበልጠዋለህ፡፡ ችሎ የሚገጥምህ፣ ገፍቶ የሚያሸንፍህ ማንም የለም፡፡ ጀግንነትህ ከተራራ የገዘፈ ነውና፡፡
በአንተ ጀግንነት በጨለማ ውስጥ ሲርመሰመሱ የነበሩት ኹሉ ብርሃን አይተዋል፣ በአንተ ጀብዱ ግርማችን ኃያል ነው ያሉት ሁሉ ተንኮታኩተዋል፣ በአንተ ገድል መነሻነት ጠላት ኹሉ ከነበረበት ሸሽቷል፡፡ ለዘላለም የጨለመች የመሰለችውን ጀንበር ለዘላለም እንዳትጠፋ አድርገህ ያበራህ፣ ለተጨቆኑት ዋስ ጠበቃ ሆነህ የተጠራህ፣ አንገታቸውን ለደፉት ደርሰህ ያኮራህ፣ አንገታቸውንም ያቃናህ፣ የጥቁርን መገኛ ምድር በኩራት ያስጠራህ፣ በዝናህ ዓለማትን ያስፈራህ፣ በጉብዝናህ ጠላትን ያፈራረስክ፣ ለአሸናፊነት ብቻ የተፈጠርክ ነህ፡፡
ብዙ ሀገራት እንደ ሀገር ሳይፈጠሩ፣ ሥርዓት ሳይሠሩ፣ በሀገር መንፈስ ሳይዘምሩ አስቀድሞ ገና መንግሥት መስርቶ፣ ግዛት አስፍቶ፣ ሥርዓት ሠርቶ፣ እውቀት አስፍቶ፣ ታሪኩን አግዝፎ በክብርና በዝና ይኖር ነበር አንተ የወጣህበት ሕዝብ፡፡ ሀገር በመመስረት፣ ሥርዓት በመዘርጋት፣ የተጨነቀን በማረጋጋት፣ የጠገበን በመውጋት፣ የተጠማን በማጠጣት፣ የተራበን በማብላት የተመሰከረለት ሕዝብ የፈለቅህ ነህና በታሪክህ ኩራ፣ የወረስከውን ታሪክ የሚመጥንም ሥራ፡፡
እሳት የጨበጠውን፣ ዙፋን ላይ የተቀመጠውን፣ ኃይል ሁሉ በእጁ የነበረውን ጨቋኝ ገዢ በባዶ እጅህ ወጥተህ፣ በወኔ ተሞልተህ፣ ሲተኩስ እየቀረብክ፣ ሲመጣ እየፎከርክ፣ ከዙፋን አውርደኃል፣ የተጫነውን የጭቆና አገዛዝ አውልቀህ ጥለሃል፣ ከቤተ መንግሥት አውጥተህ፣ እንደ ዝንጀሮ ገደል ለገደል እንዲሄድ አድርገሃል፡፡ ዛሬ ላይ አፈር ልሶ፣ ዳግም ሊመጣ ቢል እንዴት ይችልሃል?
ጠላትህ በክንድህ አይደለም በስምህ ይሸበራል፡፡ አማራ ሲባል በግርማህ ይደነግጣል፣ ፋኖ ሲባል እግር አውጪኝ ይፈረጥጣል፣ ታዲያ በክንድህ ከዙፋኑ የወረደው፣ በኃይልህ በእሳት የነደደው አሸባሪው ትህነግ ዳግም መጣሁ እያለ ነው፡፡ አማራውም ክብሩን ላለማስነካት፣ ልኩን ለማሳዬት መጣሁ ወደ አለበት ሥፍራ እየሄደ ነው፡፡ አሸባሪው ትህነግ በጦርነት ያልቻለውን ሕዝብና ሠራዊት በውሸት ያሸንፍ ዘንድ ተስፋ ሰንቋል፣ ዳሩ በግንባር የሚያመጣው ያልሰለጠነ ታጣቂ እየተለቀመ ያልቃል፣
ʺከእንግዲህ አይኖርም ነገር ማለሳለስ፣
እነርሱም አያርፉም እኛም አንመለስ” ተው ሲባሉ አልተውም፣ አትደረሱብን ሲባሉ ደርሰዋል፣ የተቀመጠላቸውን ሕግ ጥሰዋል፣ ክብር ነክተዋል፣ የትዕግስትን ወሰን አልፈዋል፡፡ አዎን አሁን ነገር ማለሳለስ አያስፍልግም፡፡ አደብ አሰይዞ መቀመጥ ይሻላል እንጂ፤ አሁን ላይ በጋራ የመመለስና የማሸነፊያ ጊዜ ነው፣ ሌላው ከድል በኋላ የሚደርስ ጉዳይ ነው፡፡ ስለ ፍቅርና ስለ ሀገር ተው ሲባሉ አላረፉምና፤ እንደ አመጣጣቸው ማስተናገድ ግድ ኾኗል፡፡
ʺለኹሉ ዘመን አለው ከሰማይ በታችም ለኾነ ነገር ኹሉ ጊዜ አለው።
ለመወለድ ጊዜ አለው፣ ለመሞትም ጊዜ አለው፣ ለመትከል ጊዜ አለው፣ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፤ ለመግደል ጊዜ አለው፣ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፣ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው፣ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፤ ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፣ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፣ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤ ለመፈለግ ጊዜ አለው፣ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፣ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ ለመቅደድ ጊዜ አለው፣ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፣ ለሰላምም ጊዜ አለው” እንዳለ ጠቢቡ የጊዜውን በጊዜው ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ʺቢመክሩት አልሰማም ቢነግሩት እምቢ አለ፣
ፋኖ እየመታው ነው ተመልከት እያለ” ፋኖ፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሻው የሚመጣውን ኹሉ ተመልከት እያለ እየመታው ነው፡፡ ፋኖን አልፎ የሚመጣ፣ ፋኖ ከሚተፋው እሳት የሚወጣ ኃይል አይገኝም፣ ኹሉም በፋኖ፣ በልዩ ኃይሉና በሚሊሻው እሳት ይለበለባል፣ እንዳልነበር ይሆናል እንጂ፤ አማራ የአባቶቹን ታሪክ የማስቀጠል፣ ክብሩን የመጠበቅና ሀገሩን የማስከበር ታላቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ኹሉም ኢትዮጵያዊያንም ከአማራው ጎን መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ አማራ በታሪኩ የሀገርን ክብር ከፍ ማድረግና ወገንን ማኩራት ነውና ይህንም ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡
ጀግናው በጦር ሜዳ ጠላቱን ሲቆላ፣ ሕዝቡ ደግሞ ስንቅና ትጥቅ እያቀበለ ከኋላ ደጀን ኾኖ ይከተላል፡፡ የጋራን ጠላት በጋራ ማጥፋት ግድ ነውና፡፡
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የኦሮሞና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ በሚለው መጽሐፋቸው ስለ አማራ ሕዝብ ሲገልጹ ʺመላዋ ኢትዮጵያ የእኛ ናት ብለው ነው አማሮች የሚያስቡት፡፡ ምክንያቱም ባለፉት በሺህዎች በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ በውትድርና ሙያቸው መንግሥታትን ሲጠብቁ እና የሀገሪቱን ዳር ድንበርና የግዛት አንድነት ሲያስከብሩ ጠንካራ የኢትዮጵያዊነትና ብሔራዊ ስሜት ገንብተዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ሀገርነት መኖር ሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን የፈፀሙት ታላቅ ጀብዱ እንደ ተጠበቀ ኾኖ ስለ እውነት ብለን እውነት ብንናገር በኢትዮጵያ ነጻነት ላይ አማሮች የመሪነት ሚና ባይጫወቱ ኖሮ ቅኝ ገዢዋ ጣልያን ኢትዮጵያን በቀላሉ ድል አድርጋ ለመያዝ በቻለች ነበር፡፡ የዚህም ምስክሩ ጣልያን ናት፡፡ የአማራን ወሳኝ ሚና በመረዳትዋ ጣልያን ከኹሉም በፊት አማራን ነበር ለማጥፋት የተነሳችው፡፡ አማሮች ከተበታተኑ ኢትዮጵያም እንደምትበታተን ጣልያኖች በሚገባ ያውቁ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን አዳክመው ለመቆጣጠር የሚሹ ከባሕር ማዶ የመጡም ኾኑ የውስጥ ኃይሎች ኹሉ ይህንኑ አድርገዋል፡፡ የአማራ ጠላት የበዛውም ለዚሁ ነው” ብለዋል፡፡May be an image of 7 people, people standing and outdoors
አሸባሪው ትህነግ አቅም አልባ ሀገር ለመፍጠር አማራውን ቢቻለው ማጥፋት፣ ካለበለዚያ ማዳከም ዋና ዓላማው ነው፡፡ ታዲያ አማራ የውጭ ጠላት ያላንበረከከውን፣ በየዘመኑ የመጣው ጠላት ከክበሩ ያላጎደለውንና ያልደፈረውን አሸባሪው ትህነግ እንደምን ችላ ትደፍረዋለች? አሸባሪው ትህነግ በጦርነት ብላው ብላው አልሆን ያላትን አማራን በውሸትና በዛቻ ታሸንፈው ይመስል ውሸቷንና ዛቻዋን ታቀላጥፈው ጀምራለች፡፡ ዋሽቶ ማሸነፍና ጉድብ ማለፍ እንደማይቻል አሳዬው፡፡
አማራ በውሸት አይደለም በጦርነት እጥፍ የሚል ግንባር የለውም፡፡ በጦር የመጣን በጦር፣ በፍቅር የመጣን በፍቅር ይቀበላል እንጂ፡፡ አሁን ላይ የአማራ ወጣት እውነቱ ጦርነቱ መሆኑን አውቆ፣ ከኋላው ስንቅና ትጥቅ ማቀበል፣ ማበረታታት፣ አካባቢውን በንቃት መጠበቅ ነው፡፡ ድሉ እውነትን የያዘው ሕዝብ መሆኑ አይቀርምና፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየአማራ ልማት ማኅበር በጎንደር ከተማ አየር ጤና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለ ሁለት ፎቅ ሕንጻ ግንባታ አስጀመረ።
Next articleበህልውና ዘመቻ ለተሰማራው ሠራዊት በኦሮምያ ክልል የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የስንቅ ድጋፍ አደረጉ፡፡