
የአማራ ሚሊሻ፣
የጠላት ማርከሻ።
ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚሊሻ ስሙ ሲነሳ ጠላትን ያርበደብዳል፣ ነበልባል ክንዱ መድረሻ ያሳጣል። ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ጠላትን ሳይቀር እንዴት ድባቅ መምታት እንዳለበት ያውቃል።
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ማን ይደፍረኛል እያለ ሲያቅራራ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በተኛበት ሲያጠቃ፣ የአማራ ሕዝብን ወግቶ ኢትዮጵያውያንን አንገት ሊያስደፋ ሲንቀሳቀስ ክንደ ብርቱው የአማራ ሚሊሻ አከርካሪውን ሰብሮ መልሶታል።
ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከአማራ ልዩ ኀይል ጋር በነበረው ድንቅ ጥምረት ኢትዮጵያን ከመፈራረስ፣ ሕዝቦቿንም ከዳግም ባርነት ታድጓል። አሸባሪው የትህነግ ቡድን ይመጻደቅባቸው የነበሩ ምሽጎችን ደርምሶ ጠላትን ደምስሷል።
የአማራ ሚሊሻ ጀግንነት ዛሬ የተፈጠረ አይደለም። ከጥንታዊት የኢትዮጵያ አርበኞች በትውልድ ቅብብሎሽ የወረሱት እንጂ። በግብርና ቢሰማራ በገፍ ያመርታል፣ እንግዳ ቢመጣ እግር አጥቦ እጅ ስሞ ይቀበላል፣ በኢትዮጵያዊ ጨዋነትም ቤት ያፈራውን ይጋብዛል። በፍቅር ለቀረበው ሟች ነው።
በክብሩና በማንነቱ ለመጣበት ግን ምህረት አያውቅም። የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር፣ ሉዓላዊነቷንም ለማስጠበቅ መስዋእት ይሆናል። ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ያሳየው ተጋድሎ ደግሞ የዚህ ማሳያ ነው።
በሕግ ማስከበር ዘመቻው አኩሪ ተጋድሎ የነበራቸው የሚሊሻ አባላት አሸባሪው የትህነግ ቡድን ዳግም ለከፈተው ጦርነት አጸፋ ለመስጠት ተሠማርተዋል።
በግዳጅ ቀጣና የሚገኙ የሚሊሻ አባላት በሽብር ቡድኑ ላይ እርምጃ ወስደው ሕዝቡን ለማሻገር በአስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የሚሊሻ አባላት እንዳሉት አሸባሪው ቡድን ከዚህ በኋላ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተስማምቶ መኖር አይችልም። እናም በአጭር ጊዜ የማያዳግም ርምጃ ወስዶ ማስወገድ ይገባል ነው ያሉት።
ሚሊሻዎቹ ወልቃይት ወረዳ ጠላት እየተደመሰሰና ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት እንደሆነም ይናገራሉ። ከሀገር መከላከያና ከአማራ ልዩ ኀይል ጋር በጥሩ ቅንጅት እየሠሩ በመሆኑ ተከዜን ጠላት የመሻገር አቅም እንደሌለው አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ- ከወልቃይት ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m