
‹‹ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛ የሽብርተኛውን ትህነግ አጀንዳ በማራመድ የትግራይ ችግር እንዲባባስ እያደረጉ ናቸው›› ዩጋንዳዊ ጋዜጠኛ ኩንጉ አልመሃዲ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጋዜጠኛው ኩንጉ አልመሃዲ ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መከላከያ ሠራዊትን ለመደገፍ እና ሽብርተኛውን ትህነግ ለማውገዝ አደባባይ መውጣታቸውን አንስቷል፡፡ ሰልፈኞቹ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥትና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል ሲል አስነብቧል፡፡ ነዋሪዎች በአደባባይ በመውጣት የዓለም አቀፍ ማኅበረሰበና ብዙኃን መገናኛዎች በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡም መጠየቃቸውን አትቷል፡፡
‹‹ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛዎች የሽብርተኛውን ትህነግ አጀንዳ በማራመድ የትግራይ ችግር እንዲባባስ እያደረጉ ናቸው›› ብሏል፡፡
አሸባሪው ትህነግ የሀገሪቱን ሥልጣን በበላይነት በተቆጣጠረባቸው ዓመታት በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና መሰል ጉዳዮች ሲፈጽም የነበረውን ግፍ ገልጿል ጋዜጠኛው፡፡ ይህ ግፍ ያንገፈገፋቸው ኢትዮጵያውያን በሕዝባዊ ትግል አሸባሪው ትህነግ ከሥልጣን መባረሩን በጽሑፉ አስነብቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ስልጣናቸውን ከያዙ ብዙም ሳይቆዩ በሀገሪቱ የነበረውን ውስብስብ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለል ጥልቅ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ተግባራዊ መደረጉንም ጋዜጠኛው ከትቧል፡፡ ከብዙ ሥራዎች መካከልም የኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን እና ጋዜጠኞችን ከእስር ለቋል፤ በስደት ያሉ ፖለቲከኞችን እና የታጠቁ ቡድኖችም በሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር እንዲሳተፉ ጥሪ በማድረግ በምርጫው እንዲሳተፉ ተደርጓል ብሏል፡፡ ምንም እንኳን አሸባሪው ትህነግ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ጊዜያት በዜጎች ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ቢያደርስም መንግሥት በይቅርታ ማለፉንም ጋዜጠኛው አስነብቧል፡፡
ለውጡ ያልተዋጠለት አሸባሪው ትህነግ እኔ ካልመራሁ በሚል ራስ ወዳድነት ሀገር ሲያተራምስ እንደነበርም አንስቷል ጋዜጠኛው፡፡
ከፌዴራል መንግሥቱ ይቀርቡለት የነበረውን የሰላም አማራጮች ባለመቀበል ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ አሳዛኝ ጥቃት ማድረሱን አንስቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በፈጣን ምላሽ እና ውጤታማ የሕግ ማስከበር ዘመቻ በአሸባሪው ቡድን ላይ ድል መቀዳጀቱን እና የተፈጠረው አደጋ በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ መመከት መቻሉንም ያስረዳል፡፡
ኩንጉ አል-መሃዲ እነዚህን እና መሰል የወቅቱ እውነቶችን በመተንተን መንግሥት በሽብርተኛው ቡድን ላይ የወሰደውን እርምጃ ምክንያታዊ እንደሆነ ሞግቷል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የውጭ የብዙኃን መገናኛ እና ግብረሰናይ ድርጅቶችን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጉዳዩን በተሳሳተ መንገድ ሲተረጉሙት ቆይተዋል ብሏል ኩንጉ አል-መሃዲ፡፡
አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛ የአሸባሪውን አጀንዳ ለማራመድ ብቻ የተፈጠሩ እንደሚመስሉም ነው የጠቀሰው፡፡ ያም ኾኖ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ለዜጎቹ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እና የመልሶ ማቋቋም ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል ብሏል፡፡
መንግሥት ያወጀውን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ባለመቀበል ሽብርተኛው ትህነግ ለክልሉ ሕዝብ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ እያገደ ነው፤ አርሶ አደሮች ተረጋግተው እርሻ እንዳያርሱ እክል ፈጥሯል፤ የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞችን ገድሏል፤ ሠራዊቱ ላይ ዳግም ትንኮሳ እየፈጸመ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት ለመሳብ የተለያዩ ሴራዎችን እየሠራ ነው ብሏል፡፡ ይህም ልብ ሊባል ይገባል ብሏል ኩንጉ አል-መሃዲ፡፡ እውነታው ይህ ኾኖ እያለ ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛ አሁንም የተሳሳተ መረጃ ለዓለም እያሰራጩ መሆኑን ገልጿል፡፡ በዚህም ኾን ተብሎ የማደናገሪያ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የጠቀሰው ኩንጉ አል-መሃዲ ይህ ግን የትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት እያስተጓጎለ መሆኑን በገጹ ጽፏል፡፡ እናም ትክክለኛውን ሁኔታ በመረዳት እና መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ በክልሉ ያለውን ሁኔታ ማሻሻል ግድ እንደሚል አብራርቷል፡፡
በአዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m