ዐቃቤ ሕግ በእነ ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል መዝገብ በ62 ሰዎች ላይ ክስ መሰረተ፡፡

238

ዐቃቤ ሕግ በእነ ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል መዝገብ በ62 ሰዎች ላይ ክስ መሰረተ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ውሳኔ በመስጠት ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና የክልልመንግስቱ ካቢኔ አባላት እንዲሁም በትጥቅ ጥቃት ላይ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው የኢፈርት ድርጅቶች፣ የግልና የመንግሥት ድርጅት አመራሮች፣ የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን አመራር አባላት፣ በትግራይ በተካሄደው ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ምርጫ ላይ ተሳትፎ ያደረጉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሊቃነ-መናብርትና የቀድሞ የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩ ታዋቂ ግለሰቦች ላይ ነው የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተው፡፡

ክሱ የተመሰረተው በሁለት የወንጀል አንቀጽ ስር ሲሆን የመጀመሪያው በኃይል፣ በዛቻ፣ በአድማና ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ኢ-ሕገመንግስታዊ ምርጫ በማካሄድ በሕገ-መንግስት የተቋቋመና እውቅና ያለው የክልል መንግስት መለወጥ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 238 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ሲሆን በሁለተኛ ክስ የፌዴራሉን መንግሥት በኃይል ለመለወጥ በማሰብ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የፌዴራል መንግሥትን በመሳሪያ ጥቃት መለወጥ የሚችል የትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ የተባለ የጦር ኃይል በማደራጀት የፌዴራል መንግሥት የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት በማድረስ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1176/2011 አንቀጽ 3/1 እና 3/2 በመተላለፍ ወንጀል ነው፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለክሱ አስረጅነት 510 የሰው ምስክሮችን እና እና 5329 ገጽ የሰነድ ማስረጃዎችን በማያያዝ ለፍርድ ቤቱ ቅርቧል፡፡

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕገ-መንግሥትና የሽብር ወንጀሎችን የሚያየው 1ኛ ችሎት ክሱን በመዝገብ ቁጥር 27128102 በመቀበል በማረሚያ ቤት የሚገኙ ተከሳሾችን ማረሚያ ቤቱ እንዲያቀርብ ቀሪ ተከሳሾችን የፌዴራል ፖሊስ መጥሪያ አድርሶ እንዲያቀርብ በማዘዘዝ ለሐምሌ 26/2013 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“አሸባሪው ሕወሓት የሚፈጽመው የሰብዓዊ ድጋፍ የማደናቀፍ ድርጊት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊወገዝ ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
Next article‹‹ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛ የሽብርተኛውን ትህነግ አጀንዳ በማራመድ የትግራይ ችግር እንዲባባስ እያደረጉ ናቸው›› ዩጋንዳዊ ጋዜጠኛ ኩንጉ አልመሃዲ