ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትግራይ ክልል ስደተኞችን ካሉበት አጣብቂኝ ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ጠየቀ፡፡

152

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትግራይ ክልል ስደተኞችን ካሉበት አጣብቂኝ ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ጠየቀ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ የፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ በማይ-ዓይኒ እና አዲ-ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ስደተኞች ያሉበትን ሁኔታ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲረዳና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡

ያጋጠሙ ችግሮችን ለማስወገድ በተደረገው ጥረት በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ 91 ሄክታር መሬት ተሰጥቶ እየተቋቋመ ያለውን መጠለያ ጣቢያ ግንባታ ለማፋጠን እየሠራን እንደሆኑ ኤጀንሲው ጠቁሟል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ግን ሰደተኞችን ከግጭቱ ቀጣና ለማውጣት ትምህርት ቤቶችን በጊዜያዊ መጠለያነት ለመጠቀም እንዲቻል ከአማራ ክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ፈቃድ እና ሙሉ ድጋፍ አግኝተናል ብሏል፡፡ አስፈላጊ የእርዳታ ቁሳቁሶች ወደ አካባቢው ተጓጓዙ ሲሆን በሂደቱም ጥቂት ዓለም አቀፍ አጋሮችም ተሳትፈዋል፡፡ ስደተኞችንም መቀበል መጀመሩን ገልጿል፡፡

የአሸባሪው ቡድን ታጣቂ ቡድኖች በትግራይ ክልል በሚገኙ በመጠለያ ጣቢያዎቹ እንቅስቃሴ ስለሚያደርጉ ስደተኞቹ ያሉበት ሁኔታ አስከፊ እና አሳሳቢ ሆኗል ነው ያለው ኤጀንሲው በመግለጫው፡፡ እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ መሰረትም ስድስት ስደተኞች በአሸባሪው ታጣቂ ቡድን ተገድለዋል ብሏል፡፡

ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ሕግ በጣሰ መልኩ ቡድኑ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከባድ መሣሪያዎችን ማከማቸት፣ ተከታታይ የሆነ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ እና የተኩስ እሩምታ በማሰማት ላይ ይገኛሉ ያለው መግለጫው በተጨማሪም ለሰብዓዊ አገልግሎት እንዲውሉ የተዘጋጁና የተቋቋሙ ጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ አምቡላንሶችን እና መሰረተ ልማቶችን ለወታደራዊ አገልግሎት እያዋሉ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ ነው ያለው፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት ሁለት ስደተኞች በጤና አገልግሎት እጥረት ህይወታቸው እንዳለፈ ሲገለጽ እናቶች ለከፋ የጤና እና የወሊድ ችግር ተዳርገዋል ተብሏል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም መጋዘኖች፣ የኤጀንሲው እና የሌሎች አጋር አካላት ንብረቶች እንደተዘረፉ ጠቅሷል፡፡ ስደተኞች ለጦርነቱ የሚውል በዓይነትና በገንዘብ መዋጮ እንዲከፍሉ እየተገደዱ እንደሚገኙም አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ስደተኞቹ ከግጭቱ አካባቢ ለመልቀቅ የሚያደርጉት ጥረት ሁሉ በአሸባሪው ቡድን የተከለከለ ከመሆኑ በላይ አሁን የሚገኙበት ሁኔታ ከእገታ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡

በተቃራኒው ስደተኞችን በጅምላ ወዳልታወቁ ቦታዎች በኃይል የማጓጓዝና እና የተወሰኑት በሕወሓት ታጣቂዎች ጥቃት ደርሶባቸው ወደ ተዘጉት ህጻፅና እና ሽመልባ መጠለያ ጣቢያዎች እንዲዛወሩ የማድረግ ሙከራዎች እንዳሉ መረጃዎች እንደደረሱትም ጠቁሟል፡፡
እስከ ዛሬ ድረስ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አሸባሪ ቡድኑ በከፈተው ጦርነት ምክንያት ማይጠብሪ ወደሚገኙት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች መግባትም ሆነ ለስደተኞች አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞች ደኅንነት ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሜ እያረጋገጠ ባለበት ሁኔታ ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ የተፈፀሙ በጭካኔ የተሞሉ ወንጀሎችን በማያሻማ ሁኔታ እንዲያወግዝ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም ስደተኞች ከሚገኙበት አደገኛ ሁኔታ እና እገታ ለመታደግ ኤጀንሲው የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፍ እና በስደተኞች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ለማጣራት የሚያከናውነውን ጥረት እንዲያግዝ ጥሪ እናቀርባለን ብሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleአሸባሪው ሕወሓት ትንኮሳውን ወደሌሎች ክልሎች በማስፋቱ የእርዳታ እህል ለማጓጓዝ መቸገሩን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ፡፡
Next article“ከታላቁ የህዳሴ ግድብ አሁንም ዓይናችንን ለአፍታ አንነቅልም” ሜጄር ጀኔራል ይልማ መርዳሳ