
የህልውና ዘመቻውን በውጤት ለመፈጸም የሚባክን ጊዜ፣ ጉልበት እንዲሁም ገንዘብ መኖር የለበትም ሲሉ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቀለሙ ሙሉነህ ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ከክልሉ ገጠር መንገድ ኮንትራክሽን ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በህልውና ዘመቻ ለሚገኙ የጸጥታ አካላት የሚውል የወር ደመወዛቸውን በመስጠት፣ ደም በመለገስ እና ስንቅ በማዘጋጀት አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡
በድጋፍ መርኃ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምትል ቢሮ ኀላፊ ቀለሙ ሙሉነህ “ዘመቻ ለህልውናችንን በውጤት ለመፈጸም የሚባክን ጊዜ፣ ጉልበት እንዲሁም ገንዘብ መኖር የለበትም” ብለዋል፡፡
ወጣት ውባየሁ አሊ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሠራተኛ ናት፡፡ ውባየሁ ለሦስተኛ ጊዜ ደም እየለገሠች ነው፡፡ ወጣት ውባየሁ “ደሜን ለወገኔ በመለገሴ ደስተኛ ነኝ” ብላለች፡፡
ሀገር ሰላም ውላ ሰላም እንድታድር ህይወቱን መስዋእት እያደረገ ላለው አካል ደምን መስጠት ያንስበታል እንጅ አይበዛበትም ብላለች፡፡
ወጣት ውባየሁ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው የተናገረችው፡፡
ወጣት ደረጀ ነገራ የክልሉ ገጠር መንገድ ኤጀንሲ ሠራተኛ ነው፡፡ ደም ከለገሱ ሠራተኞች አንዱ ነው፡፡
ወጣት ደረጀ ደም ከመለገስ ባሻገር የወር ደመወዙንም ለመስጠት መወሠኑንም ነግሮናል፡፡
ወይዘሮ ቀኑባት መስፍን መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ባለሙያ ናቸው፡፡ ሠራዊቱ ድል አድርጎ እንዲመለስ የበኩላችንን ድጋፍ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡ ስንቅ ከማዘጋጀት፣ ደም ከመለገስ ባሻገር የወር ደመወዛቸውን የሠጡት ወይዘሮ ቀኑባት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ ቀለሙ ሙሉነህ አሸባሪው ትህነግን ለመመከት ለተሠማራው የጸጥታ ኃይል ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ነግረውናል፡፡
አቶ ቀለሙ እንዳሉት ለዘመተው ሠራዊት ስንቅ እየተዘጋጀ ነው፤ ሠራተኛው በአንድ ድምጽ የወር ደመወዙን ለመስጠት ወስኗል፤ ደሜን ለወገኔ በሚል ደም የመለገስ መርኃግብር እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ ፡-ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m