
“የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር የታላቁ የኢትጵያ ህዳሴ ግድብን ከደለል ለመጠበቅ የሚያግዝ በመሆኑ ሁሉም በንቃት መሳተፍ ይገባዋል” የአማራ ክልል ምክትል ርእስ መሥተዳደር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የአረንጓዴ ዐሻራ የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርኃ ግብር በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ቤዛዊት ተራራ ተካሂዷል፡፡
በአማራ ክልል በአንድ ጀምበር ከ247 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዞ በተለያዩ አካባቢዎች የችግኝ ተከላ መርኃግብሩ እየተከናወነ ነው፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርኃግብር ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእስ መሥተዳደር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ.ር) የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር የታላቁ የኢትጵያ ህዳሴ ግድብን ከደለል ለመጠበቅ የሚያግዝ በመሆኑ ሁሉም በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለሀገር ሰላም እና ደኅንነት በግንባር የሚፋለሙ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ ቀሪው ኅብረተሰብም በችግኝ ተከላ በተደራጀ አግባብ አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ መለስ መኮንን (ዶ.ር) እንደተናገሩት በዘንድሮው ክረምት የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ከ2 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ይተከላሉ፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኞች የሚተከሉት በዓባይ ተፋሰስ አካባቢዎች ነው፡፡
በተፋሰስ አካባቢዎች የሚተከሉ ችግኞች ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ የጎላ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ የሚተከሉ ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖራቸው ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በችግኝ ተከላ መርኃግብሩ የተገኘው አርቲስት ስለሽ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) ችግኝ ተክሎ መንከባከብ ለትውልድ ታሪክ ማስተላለፍ እንደሚገባ ገልጿል፡፡ ችግኝ መትከል የሀገር ህልውና ማስጠበቅ ነው፤ ልምላሜንና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው ብሏል፡፡
በተከላው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቋል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ላይ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አርቲስቶች እና የኅብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አብዮት ከፋለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ