
ውጊያ ለመክፈት ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረገው የአሸባሪው ትህነግ ቡድን ሰብዓዊ ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን የምኒልክ ብርጌድ አስታወቀ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸባሪው ትህነግ ቡድን በወልቃይት ማይጋባ በሚገኘው የተከዜ ድልድይ አካባቢ ጥቃት ለመፈጸም ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም በአማራ ልዩ ኀይል ርምጃ እየተወሰደበት ነው።
የፌዴራል መንግሥት የተናጠል ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ አሸባሪው ቡድን ሰኔ 24/2013 ዓ.ም ውጊያ ለመክፈት ሞክሮ ነበር። በአካባቢው የተሠማራው የአማራ ልዩ ኀይል ግን ሙከራውን በብቃት በመመከት በቡድኑ ላይ የማያዳግም ርምጃ ወስዷል።
የምኒልክ ብርጌድ ዘመቻ ኀላፊ ኢንስፔክተር መኮንን ምስጋናው እንዳሉት ጠላት ሕጻናትን ያለ ምግብ በሀሽሽ እያደነዘዘ ለጦርነት እየማገደ ነው።
በአካባቢው በቂ ኀይል መሠማራቱን ያስታወቁት ዘመቻ ኀላፊው የአሸባሪው ታጣቂ ቡድን ላደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ሁሉ ተገቢ ምላሽ እንደተሰጠ ተናግረዋል። አሸባሪው ቡድን በወገን ላይ ምንም ጉዳት ሳያደርስ ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ እንዲደርስበት ተደርጓል።
ልዩ ኀይሉ ከክልሉ አልፎ ሀገራዊ ስሜት ወስዶ መሰማራቱን በመጥቀስም በአሸባሪው ቡድን ላይ የማያዳግም ርምጃ ለመውሰድ ከፍተኛ ቁርጠኝነትና በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
በሚኒልክ ብርጌድ የሁለተኛ ሻለቃ ዋና አዛዥ ኢንስፔክተር ቅዱስ በለጠ እንዳሉት ጠላት የነበረውን ኀይል ተጠቅሞ አራት ጊዜ የጸረ ማጥቃት ሙከራ አድርጎ ምንም ጉዳት ሳያደርስ ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ ደርሶበታል። ልዩ ኀይሉ አሁንም ቀጠናውን በንቃትና በብቃት እየጠበቀ እንደሆነ አብራርተዋል።
በስፍራው ስምሪት ከወሰዱ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ጠላትን የማጽዳት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።
አሚኮ በስፍራው ተገኝቶ ያነጋገራቸው የልዩ ኀይል አባላትና ኀላፊዎች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከአማራ ሚሊሻ ጋር ተቀናጅተው በጠላት ላይ ተገቢውን ርምጃ ለመውሰድ አስተማማኝ ዝግጁነት መኖሩን ገልጸዋል።
የአማራ ሕዝብም ፍየልና በግ ከማቅረብ ጀምሮ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ መኾኑም ተጠቅሷል። በጠላት ከሚናፈሱ ሀሰተኛ ወሬዎችን ራሱን በማራቅ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን ተደጋጋሚ ሙከራ በተደረገበት የማይጋባ ድልድይ አካባቢ በመገኘት የልዩ ኀይሉን፣ የሚሊሻውን እና የመከላከያ ሠራዊቱን ቅንጅታዊ አሠራር ተመልክቷል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m