“ሠራዊታችን ብሔራዊ አርማችን ነው፤ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ ነው” የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

216

“ሠራዊታችን ብሔራዊ አርማችን ነው፤ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ ነው” የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ)አሸባሪውን ትህነግ የሚያወግዝ እና የመከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ሰልፍ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የምንገኝበት ወቅት አጓጊው የለውጥ ጅማሮአችን የሚያሰጋቸው የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ሉዓላዊነትን ለመዳፈርና ሀገራዊ አንድነትን ለማጨናገፍ የሞት ሽረት እያደረጉበት ያሉበት ነው” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎች ያለፈች ሀገር መሆኗን ያነሱት ወይዘሮ አዳነች አሁን የገጠማት ፈተና አስቸጋሪ ከሚባሉ ፈተናዎች መካከል አንደኛው መሆኑን አንስተዋል፡፡

በፍቅር እንጂ በኃይል የማይንበረከከውን ሕዝባችን ይዘን፣ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ አልፈን፣ በአንድነትና በጽናት ቆመን፣ የገጠሙንን ፈተናዎች ኹሉ በድል እየተሻገርን ነውም ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።
ለአብነትም የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫና የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በድል ማጠናቀቅን አስታውሰዋል፡፡

በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተገኘው ድል ለመላው ዓለም ትምህርት የሰጠ፣ “ይበተናሉ” እያሉ ሲያሟርቱብን ለነበሩት እንደ ብረት የጠነከረ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዳለን ያሳዬ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሉዓላዊነታችን ለመዳፈር የሚቃጡ አካላትን ኹሉ ፍጹም እንደማንበገር ያስመሰከርንበት አጋጣሚ ነውም ብለዋል ከንቲባዋ፡፡ የድል ባለቤት የሆነው ጨዋውን ሕዝብም እናከብረዋንም ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ እውነትን ይዛ በጸጥታው ምክር ቤት አሸናፊ መሆኗን ያስታወሱት ምክትል ከንቲባዋ “በድሎቻችን ላፍታም ሳንዘናጋ ሥራዎቻችን ሠርተናልም” ብለዋል፡፡

የሽብርተኛው ትህነግ ቡድን በተለያዩ አጋጣሚዎች የስም ማጥፋት ዘመቻ እያደረገ ስለ መሆኑም አንስተዋል፡፡ ለስም ማጥፋት የሚጠቀምባቸው ሚዲያዎች ሕጻናትን ለጦርነት ሲጠቀም ዝም ማለታቸው ማንነታቸውን ያጋለጠና ዓላማቸውን ገሀድ ያወጣ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የሚዲያዎቹ ተግባር የሽብርተኛውን ትህነግ ኢትዮጵያን የማፍረስ ተግባር የደገፈ፣ የሉዓላዊነታችንን ቀይ መስመር ያለፈ ሆኗልም ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ እያለ ከኢትዮጵያ ላይ የሚያወራርዱት አንዳች ሒሳብ እንደማይኖራቸው አውቀው ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ እንጠይቃቸዋለንም ብለዋል፡፡

ከአንገቱ በታች የተቀበረው፣ ምላሱ ግን ያልሞተው አሸባሪ ቡድኑ በአንድ ጀንበር ኢትዮጵያን የማፈራረስና ሕዝቦቿን ሀገር አልባ ለማድረግ አፈር ልሶ ለመነሳት መፍጨርጨር ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ለንጹሐን አስቦ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ቢያደርግም ለትግራይ ሕዝብ ደንታ የሌለው አሸባሪው የትህነግ ቡድን የሰብዓዊ እርዳታ ጭምር እንዳይቀርብ እያደናቀፈ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡

ትምህርት ቤት እንጂ አፈሙዝ የማይገባቸውን ሕጻናት ለጦርነት በመጠቀም አስነዋሪ ድርጊት እየፈጸመ ነውም ብለዋል፡፡ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ብዙ ዋጋ እየከፈለ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ሠራዊቱ እየከፈለ ላለው መተኪያ የለሽ ዋጋ ለኢትዮጵያ ክብር፣ አንድነት፣ አብሮነት፣ ነጻነት የከፈለው ዋጋ መሆኑን አውቀን ከምንጊዜውም በላይ ድጋፋችንን ማጠናከር አለብንም ብለዋል፡፡ ከመከላከያ ጎን እንቆማለን፣ ድጋፋችንም እናጠናክራለን ነው ያሉት፡፡

ሠራዊታችን ብሔራዊ አርማችን ነው፣ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ ነው፣ ሠራዊታችን ምንጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ ደጀኑ፣ የሚወደውና እስከ ሕይወት መስዋእትነት የሚደርስ ደጀን ሕዝብ ያለው ሠራዊት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በእኩይ ተግባር እየተሳተፉ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ለሚፈልጉ አካላት በባንዳነት ለማስወጋት የሚያደርጉትን ጥረት ፈጽሞ እንደማይሳካ ኢትዮጵያም በእነርሱ እኩይ ሥራ የማትበታተን፣ በጸና ዓለት ላይ የተመሠረተች ሀገር መሆኗን እንዲያውቁ እንሻለንም ነው ያሉት፡፡

በተባበረ ክንድ የጸረ ኢትዮጵያ ዜማ አቀንቃኞችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመደምሰስ የኢትዮጵያን ትንሣኤ እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡ አሸባሪውና ዓለማው በኢትዮጵያ ሀቀኛ ልጆች እንደሚፈርስም አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleቺርቤዋ አምሊ 15 ጌርክ 2013 ም.አ(አሚኮ)
Next article“የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለተፋሰሱ ሀገራት እውነተኛ የትብብር ማዕከል ሆኖ ይቀጥላል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)