ʺንብ ሊባላ ሲያምረው ዙሪያውን ይወራል፣ ከሚነጋገረው ዝም ያለው ያስፈራል”

278
ʺንብ ሊባላ ሲያምረው ዙሪያውን ይወራል፣
ከሚነጋገረው ዝም ያለው ያስፈራል”
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአንድነት መዝመት፣ ለክብር መሞት፣ ለሀገር መሰጠት የቆዬ ጀግንነት ነው፡፡ ጠላቶች ቢበዙም፣ ምቀኞች ቢበራከቱም ከኢትዮጵያ ልክ አይደርሱም፣ የክብሯን ወሰን አይሻገሩም፣ የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ሊገረስሱ አይቻላቸውም፡፡ ለኢትዮጵያዊ ስለ ኢትዮጵያ ደም ከማፍሰስ፣ አጥንት ከመከስከስ የበለጠ ክብር የለውም፡፡ ለሀገር ፍቅር ለወገን ክብር ሲል በየድንበሩ ደሙን እያዘራ መጥቶ ነው ዛሬ በኩራት ታሪኩን የሚነግር።
የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም፣ ዓለት በፀሐይ ብዛት አይሳሳም፣ ድንጋይ አይቆረጠምም፣ የእሳት ዐሎሎ አይወረወርም ይህን ያውቀዋል፡፡ ራስ ገድሎ ራስ አልቃሽ፣ ራስ ዘርፎ ራስ ከሳሽ፣ የሰው ንብረት በውሸት ወራሽ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እየኖረ ኢትዮጵያን ይጠላል፣ ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ኢትዮጵያዊያንን ያነጣጥላል፣ ሀገራዊ ብልሃት፣ ሕዝባዊ አንድነት፣ ከቀደመ የመጣ ጀግንነት፣ ታሪክ ሠሪነትና፣ ዘካሪነት አይወድም፡፡ ሕዝብ እስከ ወይኑ ዛፍ ግርጌ ድረስ እንዲወስደው ይሻል እንጂ ከወይኑ ፍሬ አያስበላም፣ ሥራና መከራ ሲመጣ ከኋላ ይሰለፋል፣ ዘረፋና ጥቅም ሲመጣ ደግሞ ፊት ለፊት ያሰፈስፋል፡፡
ከተራራው ጫፍ እንዲደርስ ጀግና ይጠራል፣ በቅንነት የሚታገሉትን ከኋላ ሆኖ ጀግኖች እያለ ይከተላቸዋል፣ ከተራራው ጫፍ ሲደርስ ደግሞ ከዳተኞች ይላቸዋል፡፡ ጽናታቸው እንደ ክህደት፣ ጀግንነታቸው እንደ ስህተት ይቆጠርባቸውና ሲሻው ያስራቸዋል፣ ሲሻው ይረሽናቸዋል፡፡ የወያኔ የሕይወት ታሪክ ቢጻፍ በክፋት ተጸነሰ፣ በክፋት ተወለደ፣ በክፋት ጎረመሰ፣ በክፋት ፈራረሰ፡፡
ʺበግራና በቀኝ ውዥንብር ቢነሳም፣
የደሟን ከተማ ማይካድራን አንረሳም” በግፍ ሥለት፣ በጨካኝ ጠላት ያለቁት፣ ለዘመናት ቀያቸውን እየጣሉ የጠፉት፣ በጅምላ መቃብር የተቀበሩት፣ በለጋ እድሜያቸው ዓይናቸውን በዓይናቸው ሳያዩ የተሰለቡት፣ መመኪያ አባታቸውን፣ መደሰቻ እናታቸውን የተነጠቁት፣ ሀዘን ጨለማውን በጣለበት ባዶ ቤት የቀሩት እንደምን ይረሳሉ፡፡ የማይካድራ የስቃይ ጩኸት፣ የደም ማዕበል የበዛበት የግፍ ሌሊት እንደምን ይዘነጋል፡፡ በግፍ የገደላቸው ንፁኃን ዓይን ሳይፈስ፣ ስጋቸው ሳይፈራርስ ለሌላ በደል ራሱን የሚያዘጋጅስ ማን ይኖራል?
ዓለም በርባንን ፈትታ ክርስቶስን ሰቅላለች፡፡ በዳዩን ክሳ ተበዳዩን መቀመቅ ታወርዳለች፤ ስለ እውነት ከተበደለው ይልቅ በውሸት ስለሚያነባው ታዝናለች፣ ፍርዷንም ወደዚያው ታዘነብላለች፡፡ ለተወጋሪው ፊቷን ታዞራለች፣ ለወጋሪው ደግሞ ከንፈሯን ትመጥጣለች፡፡ ዓለም ፍርዷ የተጓደለ፣ ሚዛኗም የጎደለ ቢሆንም እውነትን አለመልቀቅና ከእውነት አለመራቅ አሸናፊ ያደርጋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ሲያጠፋ ዓለማት ዝም ይላሉ፡፡ አሸባሪው ትህነግ የሚቃዎሙ ሲነሱ ደግሞ ዓለማት ከተደበቁበት ይወጣሉ፡፡ ለዓመታት ዜጎች በግፍ ሲገድል፣ ሲያስርና ሲያሳድድ ስህተት ነው ያለ አልነበረም፡፡ በቅርቡ የተፈፀመውን የማይካድራን በደል እንኳን ለማውገዝ አልደፈሩም፡፡ የንጹሓን ደም ሲፈስስ፣ አጥንታቸው ሲከሰከስ በአሻገር አይተው ዝም ማለትን መርጠዋል፡፡ አሸባሪው ትህነግ ድረሱልኝ ባለ ጊዜ ግን እንደ አሸን ይበዛሉ፡፡
ጥንተ ጠላቴ አማራ ነው ብሎ የሚያስበው አሸባሪው ትህነግ ዛሬም ድረስ አማራን ለማጥቃት ጉድጓድ ሲጭር ያድራል፡፡ ዳሩ ʺዶሮ ጭራ ጭራ ታወጣለች ካራ “እንዲሉ ጭሮ ጭሮ መጥፊያውን አውጥቷል፡፡ አሸባሪው ትህነግ ንጹኃንን ሲገድል፣ ሲያሳድድ፣ ሕጻናትን ለጦርነት ሲያሰለፍ የዓለም ዓይኖች ሁሉ አይታያቸውም፡፡ ንጹኃንን አትገድል፣ ሀገርና ሕዝብ አትበድል ብለው የሚቃወሙት ሲነሱ ግን የዓለም ዓይን ኢትዮጵያ ላይ ይኾናል፡፡ ዓለም ፍርደ ገመድል ብትሆንም ጀግኖች ግን የኢትዮጵያን ጠላት ለማጥፋት ትግል ላይ ናቸው፡፡
ʺየፍዬል ወጠጤ ትክሻው ያበጠ ልቡ ያበጠበት፣
እንዋጋ ብሎ ለነብር ላከበት” እንዳለ ከያኙ አሸባሪው ትህነግ የማይችለውን ሕዝብና ሠራዊት እንዋጋ ይለዋል፡፡ የቀረኝ በደል፣ ያልጨረስኩት ግፍ አለና ላወራርድ መጣሁ ይለዋል፡፡ አስተዋዩ ሕዝብና ሠራዊት ግን ሲመጣ ከንፁኃን ጉያ ትወሸቃለህ ዝም ስልህ ደግሞ በአፋፍ ጫፍ ሆነህ ሞት ትጠራለህ እባክህን ዝም በል እያለው ነው፡፡
አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያዊያን እንዲለያዩ አያሌ ሥራዎችን ቢሠራም በሞቱ ላይ አንድነታቸውን ለማጽናት፣ አንድነታቸውም በቀላል ነገር እንደማይበጣጠስ ለማሳዬት፣ በጋራ ቆመው በጋራ አልመው ሊያጠፉት ተነስተዋል፡፡ ጠላቴ ነህ የተባለው አማራም ጠላቱን ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአማራ ሚሊሻና ፋኖ ሕዝብን ደጀን አድርጎ የአሸባሪው ትህነግን ፊት ለመመለስ፣ ከምሽጉ እያወጣ ለመደምሰስ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርጎ ለማንገሥ ዘመቻ ላይ ነው፡፡
ʺደህና ጎበዝና ነበር አንድ ናቸው
ሰው ደርሰው አይነኩም ካልደረሱባቸው” እንደተባለ አማራ ካልደረሱበት ደርሶ አይነካም፣ ከደረሱበት ግን ክብሩን አያስነካም፡፡ በፍቅር፣ በመከባበር፣ በጋራ በመኖር ያምናል፡፡ ደርሰው ከነኩት፣ ክብሩን ከገፉት ግን እንደ አንበሳ አግስቶ፣ እንደ ነብር ተቆጥቶ ይነሳል፡፡ ያን ጊዜ ለጠላቱ ወዮለት፣ እንደ ማዕበል ያለብሰዋል፣ እንደ መብረቅ ይመታዋል፣ እንደ ውቅያኖስ ያጠልቀዋል፡፡ ክንዱን ያቀምሰዋል፣ ጀግንነቱን ያሳየዋል፡፡
አማራ ለአሸባሪው ትህነግ መቀበሪያ እንጂ መኖሪያ የሚሆን መሬት፣ ትህነግን የምንመክትበት ጋሻ እንጂ የሚሸከም ትክሻ የለንም፣ የበደለንን ረስቶ፣ ያደረገውን ዘንግቶ ከመጣ ዘመኑን እንቋጨዋለን፣ ግብዓተ መሬቱን እንፈጽመዋለን እያለ ነው፡፡ ለዚያም ይሆን ዘንድ ወያኔ ይገባባቸዋል ብሎ የሚያምንባቸውን በሮች ሁሉ ዘግቷል፡፡
ʺየአንበሳው በሽታ ሕመሙ እንደምን ነው፣
እያንዘፈዘፈ እየቀሰፈው ነው” እንደተባለ አንበሳው በግንባር ዘምቶ የሚመጣውን ሁሉ በግርማው እያንዘፈዘፈ፣ በአፈ ሙዙ እየቀሰፈ ልኩን እያሳዬው ነው፡፡ ለጠላት የሚባክን ጥይት፣ የሚስት ሠራዊት የለምም እያለ ነው፡፡ ከአባት እንደወረሰው አነጣጥሮ እየተኮሰ፣ ጠላቱን በአሻገር እየመለሰ ነው፡፡
ʺንብ ሊባላ ሲያምረው ዙሪያውን ይወራል፣
ከሚነጋገረው ዝም ያለው ያስፈራል” አማራ ጠላቱን ዙሪያውን ይዟል፣ ጠላቶቹ ሽንፈቱን ሊያወሩና ሊመኙ ይችላሉ፡፡ እርሱ ግን ታግሶ ተነስቷልና ከትዕግስትና ከአስተውሎት የተነሳው ጀግንነቱ ለድል እንደሚያደርሰው ያምናል፡፡ ያንንም እያደረገ ነው፡፡ ከወያኔ ማውራትና መንጫጫት ይልቅ የአማራው ዝምታ ያስፈራል፡፡ በዝምታው ውስጥ ጀግንነት፣ አይሸናፊነት፣ አርቆ አሳቢነት አለውና፡፡ አማራ ʺአሥር ጊዜ ለካ አንድ ጊዜ ቁረጥ” ይላል፡፡ ሳይለካ አይቆርጥም፣ ከቆረጠው የተቆረጠው ዳግመኛ አያቀጠቅጥም፣ ለክቶ ያሰምራል፣ አስምሮ ይቆርጣል፡፡
የአሸባሪው ትህነግ አፈር ልሶ እነሳለሁ ማለት ዳግም ማይካድራ እንደሚያመጣ ያውቀዋልና ለጩኸታቸውና ለዛቻቸው የሚመጥነውን ለመስጠት ወደ ሥፍራው አቅንቷል፣ ቦታውን አዘጋጅቷል፣ የተወለወለ አፈሙዝ፣ ትጥቁ የማይፈታ ደህና ጎበዝ አለና ብቅ ሲል እንቅ እያደረገ መውጫ አሳጥቶታል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“አሸባሪው የትህነግ ጁንታው ቡድን በክልላችንና በሀገራችን ላይ እየፈፀመ ያለውን የወረራና የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ በቂ ምላሽና የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ ቀጥሏል” የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት
Next articleየአሸባሪውን ትህነግ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።