“ኢትዮጵያ ወደብ ካላቸው ሀገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነት አብሮ ለመልማትና የሕዝቦችን ትስስር ለማጠናከር ሰፊ እድል ይፈጥራል” የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ

471
“ኢትዮጵያ ወደብ ካላቸው ሀገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነት አብሮ ለመልማትና የሕዝቦችን ትስስር ለማጠናከር ሰፊ እድል ይፈጥራል” የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገራት ያሉ አማራጭ ወደቦችን የመጠቀም ዕድሎቿን ማስፋቷ ኢኮኖሚውን ከመደገፉም ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም ያሏትን እድሎች የማስፋት ተግባራት እያከናወነች ነው።
ኢትዮጵያ በወጪና ገቢ ንግድ ከጂቡቲ ወደብ በተጨማሪ የታጁራ፣ በርበራና ፖርት ሱዳን ወደቦችን እየተጠቀመች እንደምትገኝም ገልጸዋል።
እያደገ የመጣውን የገቢና ወጪ ንግድ መሸከም የሚያስችል ተጨማሪ ወደብ መጠቀም እንዳስፈለገ ጠቁመዋል። የላሙ ወደብን ለመጠቀም ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ እንደሆነም ተናግረዋል።
ሀገሪቷ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም በመቻሏ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷን እንድታሰፋ እድል የሚፈጥር መሆኑንም አመላክተዋል። ወጪን በመቀነስም ለልማት ማዋል የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያመቻች መሆኑን አብራርተዋል።
ለአብነትም በዚህ ዓመት በታጁራ ወደብ ብቻ ከ700 ሺህ ቶን በላይ የድንጋይ ከሰልና ከ200 ሺህ ቶን በላይ ካርጎ መግባት በመቻሉ በጂቡቲ ወደብ ላይ ይወሰድ የነበረውን ጊዜ እንዳሳጠረ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ወደብ ካላቸው ሀገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነት አብሮ ለመልማትና የሕዝቦችን ትስስር ለማጠናከር ሰፊ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ከወደብ አገልግሎቱ በተጨማሪም በመሰረተ ልማት ሥራዎችም መንገዶች ወደሌሎች የቀጣናው ሀገሮች መሸጋገሪያ እንዲሆኑ በማድረግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ ይበልጥ የሚጠናከርበት ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከካይሮ እስከ ኬፕታውን የሚዘረጋው የመንገድ አካል የሆነው ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ሆኑ።
Next articleበአፋር ክልል በኩል ትንኮሳ የፈጸመው የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ተደመሰሰ።