የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መንግሥት እና የስድስት ከተሞችን ፖርታሎች አልምቶ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረጉን ገለጸ፡፡

154
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መንግሥት እና የስድስት ከተሞችን ፖርታሎች አልምቶ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረጉን ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በመጀመሪያው ዙር ፖርታል የለማላቸው ከተሞች አዲስ አበባ፣ ባሕርዳር፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ፣ ሃዋሳ እና አርባ ምንጭ ናቸው።
ፖርታሎቹ የየከተሞቹ አጠቃላይ ታሪክ፣ የከተሞቹ አመራሮች ከእነ አድራሻቸው፣ ከተማው ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎት፣ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቦታዎች፣ የአገልግሎት መስጫ ሰዓት፣ ሊጎበኙ የሚችሉ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች፣ በከተሞቹ ውስጥ ያሉ ፕሮጀክቶች፣ የሚያበቁበት ጊዜ፣ የአደጋ ጊዜ ስልኮች፣ ሰነዶች፣ ደንበኞች ለከተማዎቹ ባለሙያዎች ጥያቄ በቀጥታ የሚጠይቁበትና ምላሽ የሚያገኙበት እና ሌሎችንም መረጃዎች አካትተው የሚይዙ ናቸው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ነዋሪዎች ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩ ለማድረግ በቂ መረጃ የሚያገኙበት ሥርዓት መዘረጋት እንዳለበትና የዚህ አንዱ አካል ደግሞ የከተሞች ፖርታል መሆኑን አንስተዋል።
ከተሞች ለቴክኖሎጂ ቅርብ እየሆኑ በሄዱ ቁጥር ትልልቅ ባለሃብቶችን መሳብ የሚችሉና ለዜጎቻቸው የተመቹ የሚሆኑበት እድል ይፈጠራል ብለዋል።
የመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ያለበት ደረጃ ላይ ማብራሪያ የሰጡት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲ ልማት ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል አብዮት ሲናሞ (ዶ.ር) ለዜጎች ተዓማኒ፣ ቀልጣፋና የማይቆራረጥ አገልግሎት ለመስጠት መንግሥት የዘርፉን ማሻሻያዎች እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በባሉበት (ኦንላይን) አገልግሎት ዘርፍ 17 ተቋማት አገልግሎታቸውን ኦንላይን እየሰጡ ነው ያሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ በዚህም 124 አገልግሎቶች በኦንላይን እየተሰጡ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ጀነራል አብዮት ባዩ (ዶ.ር) የከተማ አስተዳደሮቹ ፖርታሎቹን በማዘመን መረጃ ከመስጠት አልፈው ነዋሪዎቹ ጥያቄ የሚጠይቁበትና ሌሎች አገልግሎቶችን ማግኘት የሚችሉበት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የተገልጋዮችን ሐሳብ መቀበል፣ ቅሬታ ማስተናገድ፣ ማስተካከያዎችን በማድረግ ማስተካከያ ስለማድረጋቸው ማረጋገጫ መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል።
ከተሞቹ በሀገር ውስጥ አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ጥረት ማድረግና በተወዳዳሪነታቸው ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዲሆኑ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የፖርታሎቹ አጠቃላይ ገፅታ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ከፍተኛ የስትራቴጂ አማካሪ ፍቃደ ጌታሁም (ዶ.ር) ፖርታሎች ቀጣይነት ባለው መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ የመረጃ ባለሙያዎችን በመመደብ ወቅታዊ መረጃዎችን እንዲሰጡ ማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።
ትክክለኛ መረጃዎችን በመስጠትም የየከተሞቹ ብቸኛ ታማኝ የመረጃ ምንጭ ኾነው ማገልገል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የየከተሞቹ ከንቲባዎችና የየክልሎቹ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊዎችም (የአዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ ሃዋሳ፣ አዳማ እና አርባ ምንጭ) ፖርታሎቹ ሳይቆራረጡ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ ይሆን ዘንድም ከሚኒስቴሩ ጋር የተፈፃሚነት የቃል ኪዳን ፊርማ ተፈራርመዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የትህነግ ፕሮፓጋንዳ አንዱ ማደናገሪያ”
Next article“በሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት የተጎዱ የሠራዊት አባላት ለጀግንነታቸው የሚመጥን ክብካቤና ድጋፍ እንዲያገኙ እየሠራን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ