“የትህነግ ፕሮፓጋንዳ አንዱ ማደናገሪያ”

186
“የትህነግ ፕሮፓጋንዳ አንዱ ማደናገሪያ”
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2013 ዓ.ም(አሚኮ) ግራ ዘመም ኀይሎች ለሽምቅ ውጊያ “ፕሮፖጋንዳ ትልቅ ኀይል ነው” የሚል መከራከሪያ አላቸው። ፕሮፓጋንዳ ሲባል አንድን ጉዳይ አስፍቶ እና ለጥጦ ማሰራጨት በሚል አግባብ ሊተረጎም ይችላል። ለዚህም ይመስላል ትህነግ ከመነሻው ጀምሮ ፍጹም ምናብ ወለድ እና እውነት ጠል ድርጅት ኾኖ ሳለ በሚያሰራጨው ፕሮፖጋንዳ እውነትን የሚከተል ድርጅት ለመመስል የሞከረው።
ትህነግ በበርሃ የትግል ወቅት እንደ “ድምጸ ወያኔ” ሬዲዮ፣ “ወይን”፣ “ታጠቅ” እና በመሳሰሉ ጋዜጦቹ ጭምር ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ሕዝብን ያደናግር እንደነበር ይታወቃል።
በውሸት በትረ ስልጣኑን ከተቆናጠጠ በኋላም በፖለቲካው እና በልማት ሥራዎች ጭምር ምናባዊ ድርስት በመጻፍ ሲቆጣጠራቸው በነበሩ ልሳኖቹ የተለመደውን ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ሕዝብን ሲያደናግር፣ የማኅበረሰቡን የእውነተኛ ታሪክ እና እሴት ጭምር ሲሸረሽር ቆይቷል።
ትህነግ ከአራት ኪሎ ተባሮ መቀሌ ከመሸገ በኋላም በመከላከያ ኀይሉ ላይ በፈጸመው ክህደት ምክንያት በፌዴራሉ መንግሥት የሕግ ማስከበር ዘመቻ በተወሰደበት ጊዜም “ገደልኩ” እና “ማረኩ” ያለው የወታደር ቁጥር ቢደመር ሀገሪቱ ካላት ሠራዊት በላይ ይኾናል ቢባል ማጋነን አይኾንም።
አሁንም መንግሥት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ተከትሎ ትህነግ ባደረገው ትንኮሳ በ”ትግራይ ሚዲያ ሀውስ”፣ በዲጂታል ሠራዊቱ እና በመሳሰሉ ልሳኖቹ የሚያሰራጨው የሀሰት በሬ ወለደ ወሬ የቡድኑን የቀድሞ ባህሪ ለማይረዳ እና ለማያውቅ ሰው በትንሹም ቢኾን መደንገጡ የማይቀር ነው።
ትህነግ አሁንም በእነዚህ ልሳኖቹ ክልሎችን ከክልሎች እና ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ለመከፋፈል ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ጦርነቱም ክልሎችን እንደማይመለከት አድርጎ እያሰራጨ ይገኛል።
አሚኮም እውን ይህ ጦርነት የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አይወከልም? ሲል የወልድያ ከተማ ነዋሪዎችን ጠይቋል። ትህነግ በኢትዮጵያ ሕዝቦች የተነጠቀውን ስልጣን መልሶ ለመጨበጥ ጦርነት ከፍቶ ሲያበቃ መሬት ለማስመለስ ነው እያለ በልሳኖቹ እያሠራጨ ያለው የሀሰት መረጃ አዲስ ሳይኾን ቀደሞ ጫካ በነበረበት ጊዜ ጀምሮ እንደ አንድ መታገያ ስልት አድርጎ ሲጠቀምበት እንደነበር ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት ትህነግ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የአማራን ሕዝብ ብቻ ሳይኾን ኦሮሞን ከሱማሌ፣ አፋሩን ከሱማሌ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው እንዳይተማመኑ በማድረግ ሲያባላ የነበረ ዘራፊ ቡድን ነው።
በዚህ ወቅትም ከአማራ ሕዝብ አልፎ በአፋር ሕዝብ እና የሀገር አለኝታ በኾነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት የፈጸመ አሸባሪ ቡድን በመኾኑ ጥቃቱ በሀገር ህልውና ላይ የተቃጣ እንደኾነ አስገንዝበዋል። በዚህም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ይህንን ቡድን በጋራ ሊታገሉት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሕዝቡም በጦር ሜዳ ከመፋለም ጀምሮ የቁሳቁስ፣ የገንዘብ እና የሞራል ድጋፍ በማድረግ ጭምር ትግሉን ሊያጠናክር እንደሚገባ አንስተዋል። አስተያየት ሰጭዎች ትህነግ በጫካ እና ባለፉት 27 ዓመታት በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የጫነው “መንግሥታዊ” ውሸት የታወቀ ነው ብለዋል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ሥራ ይጠይቃል ያሉት ነዋሪዎች ከሚሠራው ሥራ በፊት ግን የችግሩ ምንጭ የኾነውን ትህነግ ማድረቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ለተለያዩ ጄኔራሎችና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የሥራ ምደባ ሰጡ።
Next articleየኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መንግሥት እና የስድስት ከተሞችን ፖርታሎች አልምቶ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረጉን ገለጸ፡፡