
“የግድቡ ግንባታ ለፍጻሜ እንዲበቃ የክልሉ ህዝብና መንግሥት ድጋፋቸውን ያጠናክራሉ” ርእስ መሥተዳደር ደስታ ሌዳሞ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሰፊውን ሕዝብ ከጨለማ የሚያወጣ በመሆኑ ቀሪው ግንባታ ለፍጻሜ እንዲበቃ የክልሉ ኅብረተሰብና መንግሥት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የሲዳማ ክልል ርእስ መሥተዳደር ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።
ከሲዳማ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን በመደገፍና የአሸባሪውን ሕወሓት ጥቃት የሚያወግዝ ሰልፍ ዛሬ በሀዋሳ ሚሊኒየም አደባባይ አካሂደዋል።
በዚህ ወቅት ርእሰ መሥተዳድሩ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያዊያን ከልጆቻቸው ጉሮሮ ጭምር እየነጠቁ ግድቡን ለመገንባት ተረባርበዋል። ሆኖም በሂደቱ አያሌ ፈተናዎች መግጠሙን ጠቅሰው በተለይ ስልጣን ተቆናጥጦ የነበረው የሕወሓት ጁንታ በግድቡ ስም ገንዘብ እያሰባሰበ ከፍተኛ ዘረፋ ማካሄዱን አመልክተዋል። በዚህ ኹሉ ዜጎች ተስፋ ሳይቆርጡ ገንዘባቸውን አውጥተው ግድቡ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያዊያን ህልም እንዲሳካ የለውጡ መንግሥት በግድቡ ዙሪያ የነበረውን ችግር በማጤንና ቆራጥ እርምጃ በመውስድና ከውጭ የሚደርስበትን ጫና በመቋቋሙ ግድቡ ውኃ እንዲይዝና ወደ ምርት እንዲሸጋገር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።
ይህም የለውጡ ከፍተኛ ተምሳሌትና ትሩፋት አድርጎ መውሰድ እንደሚቻል ርእሰ መሥተዳድሩ አውስተዋል።
ግድቡ ሰፊውን ሕዝብ ከጨለማ የሚያወጣ በመሆኑ ቀሪው ግንባታ ለፍጻሜ እንዲበቃ የክልሉ ኅብረተሰብና መንግሥት ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉበትም አስታውቀዋል።
ጁንታው “ከጎረቤት ሀገራት ተልዕኮ ወስዶ የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል በሰፊ ከመንቀሳቀስ አልፎ ዛሬ ላይ በሀገሪቱ ላይ ጥቃት ማድረሱ” በቃህ ሊባል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ “የአሸባሪው ርዝራዠመልሶ እንዳይበቅል በማድረግ ሰላማችንንና ልማታችንን አስተማማኝ ለማድረግ ከሕዝባችን ጋር ተባብረን እንሠራለን” ብለዋል።
በተለይ የክልሉ ሕዝብ የሀገሪቱን ዳር ድንበር ለማስከበር ሌት ተቀን እየደከመ የሚገኘውን መከላከያ ሠራዊት ለማጠናከር የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲያጎለብትም ርእሰ መሥተዳድሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በበኩላቸው፤ ግድቡ ድህነትን ለማሸነፍ ዓይነተኛ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ የተካሄደው ሰልፍ ዋና ዓላማ ሀገሪቱን ከልማቷ ማስቆም እንደማይቻል ለወዳጅም ለጠላትም ለማስገንዘብ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ከሰልፉ ተካፋዮች መካከል አቶ ከበደ ባይሶ በሰጡት አስተያየት፤ በግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መደሰታቸውን ገልጸው ፤ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
አቶ ለገሠ ነጋሽ የተባሉ የሰልፉ ተሳታፊ በበኩላቸው፤ ግድቡ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከሚያስገኘው ጥቅም ባሻገር ዜጎችን በአንድነት በማስተሳሰር መሠረት የጣለ በመሆኑ እስከፍጻሜው ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ለመግለጽ በሰልፉ መካፈላቸውን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ፀዳለ ጌታቸው ናቸው።
የሰልፉ ተካፋዮች ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ በሀዋሳ ሚሊኒየም አደባባይ በመገኘት ለግድቡ ድጋፋቸውን በመግለጽ፤ የአሸባሪውን ሕወሓት ጥቃት አውግዘዋል፡፡ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አጋርነት በሰጡት አስተያየትና ባሰሙት መፈክር አረጋግጠዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m