
ኢብራሂም፡ የነብዩሏህ ልጅ ነውና፤ እስከ መስዋዕትነት ድረስም ታዟልና ለነብይነት ተመረጧል!
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) እናቱ አስተዳደጓ ቅንጦት የበዛበት እንደነበር የኋላ ታሪኳ ያሳያል፡፡ ነገር ሁሉ ሞልቶ በተረፈበት የግብጽ አብያተ መንግሥታት እና በዓባይ ወንዝ ዳርቻ ተቀማጥላ ያደገች ሴት ነበረች፡፡ ከፍልስጤም እስከ ዮርዳኖስ፤ ከሶሪያ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ ቦታዎች በሚደርሰው የሻም ምድርም ኖራለች፡፡ ልምላሜ በበዛበት እና ውኃ በሚፈልቅበት ቦታ ያደገችው እናት ሃጀር ነብይ ይሆን ዘንድ የሚመረጠውን ልጇን ይዛ በሻም ምድረ በዳ ትወጣ እና ትወርድ ዘንድ በአሏህ ግድ የምትሰኝበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ያ ጊዜ የቀረበ ይመስላል ያለመከራ አሸናፊነት፤ ያለጥረት ውጤት አይመጣም፡፡
አባቱ የአሏህ አገልጋይ እና ነብይ ናቸው፡፡ ነብዩ ኢብራሂም አሏህ አብዝቶ ይወዳቸዋልና የፍቅራቸውን ጥግ፣ የታዛዥነታቸውን ብርታት እና የአገልግሎታቸውን ጽናት ሊፈትነው ይወዳል፡፡ በመጨረሻም ታላቁ ነብይ ኢብራሂም ቅን አገልጋይ፣ ታናሹ ነብይ ኢስማኤል ታዛዥ እናት ሃጀር የጽናት ተምሳሌት ሆነው ይወጣሉ፡፡ ለምድረ በዳዋ ቅድስት ከተማ መካ ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች ተብለው ይመዘገባሉ፡፡
አሏህ ስለነብዩ ኢስማኤል ሲልም የዘምዘም ውኃን ለፍጥረቱ ሁሉ ይቸራል፡፡ ነብዩ ኢብራሂም ሃጀርን እና ልጃቸውን ኢስማኤልን ይዘው ከሻም ሀገር ተነስተዋል፡፡ የጉዟቸው መዳረሻ ደግሞ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ቅድስት ከሚባሉት አራት ከተሞች መካከል አንዷ እና ቀዳሚዋ የመካ ምድር ነበረች፡፡ ለጉዞ ሲነሱ የመፃዒው ጊዜ ነብይ የወቅቱ ሕፃን የነበረው ኢስማኤል ጡት ያልጣለ ጨቅላ ነበር፡፡ ኢብራሂም ሐጀርንና ሕፃኑን ኢስማኤልን ተምር ከያዘች ትንሽ አቅማዳና ውኃ ከያዘች ኮዳ ጋር ሰው በሌለበት የመካ ምድረበዳ ላይ ተዋቸው፡፡
በአካባቢው ሕይዎት ያለው ነገር ፈጽሞ አይታይም፤ የሰማይ አዕዋፍት፣ የምድር እንስሳት እና እፅዋት በዚህ ምድረበዳ ጉዳይ ያላቸው አይመስሉም፡፡ ነብዩ ኢብራሂም በዚህ ምድረ በዳ የአብራካቸውን ክፋይ ልጃቸውንና ሐጀርን ትተዋቸው ወደ ኋላ በመዞር ወደ ሻም ምድር ገሰገሱ፡፡ ጉዳዩ ታላቅ ጭካኔ ይመስላል፡፡ የኢስማኤል እናት ሐጀር ሁኔታውን ለማመን የሚከብድ በሚመስል እይታ ዙሪያ ገባውን ለመቃኘት ሞከረች፡፡ ቦታው ምንም ነገር የማይታይበት እና ምንም ድምፅ የማይሰማበት እጅግ አስፈሪ ምድረ በዳ ሆነባት፡፡ በአካባቢው ምንም አይነት የአደም ዘር አልነበረም፡፡ ሐጀር ተነሳችና ትቷት የሚሄደውን ባሏን ለመከተል አሰበች… ግን አላደረገችውም፡፡
እናት ሃጀር “ኢብራሂም ሆይ ወዴት ትሄዳለህ?” ስትል ተጣራች፡፡ ነብዩ ኢብራሂም ግን መልስ አልሰጧትም፡፡ መልሳ መላልሳ ተጣርታለች መልስ ግን አላገኘችም፡፡ ሃጀር በመጨረሻም “ኢብራሂም ሆይ ነገሩ ከወደ አሏህ ነው እንዴ?›› ስትል ጠየቀቻቸው፡፡ አሁን ከነብዩ ኢብራሂም መልስ አገኘች፤ እንግዲያውስ አሏህ በቂየ ነው በል ሂድ አለች፤ ወደ ልጇም ተመለሰች፡፡ ሐጀር ከያዘችው ጥቂት ውኃ ልጇን አስጎነጨች፤ ጡቷንም አጠባች፡፡ ብዙ አልቆየም የያዙት ውኃ አለቀ፤ የእናቲቱም ጡት ደረቀ፡፡ በዚያ ምድረ በዳ እናትና ልጅ ውኃ ጥም በረታባቸው፡፡ ሕፃኑ ኢስማኤል ከርሃቡ እና ውኃ ጥሙ ማየል የተነሳ ተዝለፈለፈ፡፡ ከውኃ ጥማቱ ብርታት የተነሳ ጣቱን ይጠባል፤ ሲብስበት ደግሞ መሬቱን በእጅና እግሩ ይደበድባል፤ አምርሮ ያለቅሳል፤ ሃጀር የእናት አንጀቷ አልችል ሲላት ዙሪያ ገባዋን ትቃኛለች፤ ግን ምንም ጠብ የሚልላት ነገር የለም፡፡

ሃጀር በምድረ በዳው ውስጥ ተስፋ ያደረገችው አሏህን ነበር፡፡ የልጇን ነፍስ ለማቆየት ውኃ ፍለጋ ተራራ ወጥታ ሸለቆ ትወርዳለች፡፡ ተጣድፋ ወጥታ ተጣድፋ ትወርዳለች፡፡ የሚረዳት ፍጥረት የልጇን እስትንፋስ የሚያቆይ የውኃ ጠብታ አጥታ ትብከነከናለች፡፡ በሶፋና በመርዋ ኮረብታማ ቦታዎች ለሰባት ጊዜያት ያክል በጥድፊያ ወጥታ በጥድፊያ ወርዳለች፤ ጠብ የሚል ውኃ ባታገኝም፡፡ ሃጀር ድካሟ ፍሬ ሊያፈራ ሲቃረብ በሰባተኛው ዙር መርዋ ተራራ ላይ ባለች ጊዜ የሆነ ድምፅ ሰማች፡፡ ለራሷም “እሽሽ…እሽሽ…” አለችና ድምፁን ወደሰማችበት አቅጣጫ ጀሮዎቿን አቀናች፡፡ የሰማችው ድምፅ አልደገምላት ሲልም “ሆነ ድምፅ ሰምቻለሁ… ረጂ ከሆንክ እባክህን ድረስልኝ…እርዳኝ” ስትል ተማጸነችው፡፡ ወደ ልጇ ዘወር ስትልም አንድ መልአይካ በክንፎቹ መሬት ሲቆፍር ተመለከተች፡፡ እርሱም ውኃው ከመሬቱ እስኪፈልቅ ድረስ በክንፎቹ ቆፈረው፡፡ የሕፃኑ እናት ሃጀር ደስታ ፈንቅሏት ወደ ውኃው ፈጠነች፡፡ ፈስሶ እንዳያልቅባትም በአፈርና ድንጋይ ገደበችው፡፡
ሃጀር የትዕግስቷን ጥፍጥና ለልጇ አቀመሰች፡፡ ባሮቹን በሚያክመው ወዳጆቹን በሚሸልመው አሏህ ስለትዕግስቷ፣ ስለጽናቷ እና ስለድካሟ “የዘምዘም ውኃ” ፈልቆላት የልጇን ጥም አረካች፤ እርሷም ተጎነጨች፡፡ ኢብራሂም እና ሃጀር ያ የመከራ ዘመን አልፎላቸዋል፤ በአባቱ የሚጎበኝበት እና በፈጣሪ የሚፈተንበት ደርሷል፡፡ ነቢዩ ኢብራሂም ለልጅ ከፍተኛ ጉጉት ቢኖራቸውም ልጅ ሳያገኙ 120 ዓመታትን ቆይተዋል፡፡ ከብዙ ልመና በኋላ ግን በእድሜያቸው ማምሻ ላይ ኢስማኤል ከፈጣሪ ተቸራቸው፡፡
በስተርጅና ዘመን ባገኙት ልጅ ደስተኛ የነበሩት ነብዩ ኢብራሂም በደስታ መጀመሪያቸው ላይ ግን ትልቅ ፈተና ተደቀነባቸው፡፡ በሕልማቸው ልጃቸው እንዲሰዋ ተጠየቁ፡፡ አዘኑ፤ የአሏህን ትዕዛዝ ለልጃቸው ነገሩት፤ ኢስማኤልም በፈጣሪ ትዕዛዝ እንደሚስማማ ነገራቸው፡፡ ትዕዛዙን ለማስፈጸም አባት እና ልጅ ከመካ ከተማ አረፋ ተራራ ደረሱ፡፡ ኢስማኤልም ‘‘አባቴ ፊቴን እያየህ አላስጨክን እንዳይል፤ ስሰቃይም ዓይተህ እንዳትተወኝ ፊቴን ወደመሬቱ አዙረህ እረደኝ’’ በማለት ታዛዥነቱን በእዝነት አረጋገጠ፡፡
የአባት እና ልጅ ለፈጣሪ አብዝቶ መታመን እና መታዘዝ ታዓምራትን አሳየ፤ ስለኢስማኤል መስዋእትነት ፋንታ በግ ከሰማይ በስጦታ ወረደ፡፡ ዕለቷም የዒድ አል አድሃ በዓል በመባል ትከበራለች፡፡ ኢድ አል አድሃ መስዋእት የሚደረግበት ቀን ነው፡፡ ነብዩሏህ ኢብራሂም የሰባት ዓመት ልጃቸውን ለእርድ ያቀረቡበት ጊዜም ነው፡፡
በዓሉን የእስልምና እምነት ተከታዮች በመሰባሰብ እና ሶላት በመስገድ ያከብሩታል። እንደነብዩ ኢብራሂም፣ ነብዩ ኢስማኤል እና እናቱ ሃጀር የዚህ ወቅት ተጓዥም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳይፈተን ያች ቅድስት ከተማ መካ በኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሚሊዮን በሚቆጠሩ አማኞች ትዘየር ነበር፡፡ ከዘምዘም ውኃ ጠጥተው ከመስዋእቱ እርድ ተከፋፍለው ከአሏህ በረከትን ተነይተው ይመለሱ ነበር፡፡ ዘመን አልፎ እና ኮሮና የዓላማችን የጤና ስጋት መሆኑ ሲቀየር አሏህ ቢሻ ዳግም ኢድን በመካ ደምቆ ሲከበር እናያለን፡፡ ኢድ ሙባረክ!
ምንጭ፡- ልዩ ልዩ አስተማሪ ኢስላማዊ ታሪኮችን ዋቢ አደረግን
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
