
የጋራ ሀገር ስጋት የሆነውን አሸባሪ ቡድን ለማስወገድ ኢትዮጵያውያን የጋራ ትግል እንደሚጠበቅባቸው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አስገነዘቡ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ በምዕራባውያን ጋሻ ጃግሬነት የሀገሪቱን በትረ ስልጣን ከጨበጠ ከጥቂት ወራት በኋላ የቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ ትህነግ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ለመቅበር ይከተለው በነበረው የዘውግ ፖለቲካ ነው እውነቱን ተናግረው ነበር።
ኮሎኔሉ በምክር ቤቱ “ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ዕቅድ አሸባሪው ትህነግ አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝ እና ሊታመን የማይችል ነው ነበር ያሉት በወቅቱ።
በጊዜው የሰከረ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ፣ በብሔር እና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ ቡድኖችን ሀገር ምሩ ብሎ ኀላፊነት ማሸከም ለእኔ ከአዕምሮ በላይ ነው …” ብለው እንደነበር ተሰንዶ ይገኛል።
“አሸባሪው ትህነግ ከኢትዮጵያ ሀገረ ግንባታ ጋር አብሮ የማይሄድ፣ ሌሎች ሀገሮችን ያፈራረሰ ስታሊናዊ የልዩነት መስመር ያሰመረው የሚፈልጋትን ሀገር እስከሚመሠርት በከፋፍለህ ግዛ ስልት በስልጣን ላይ ተፈናጥጦ ለመቆየት ነው” በማለት ሀሳባቸውን ገልጸው ነበር።
በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር ሽዓለሙ ስዩም ትህነግ ባለፉት 27 ዓመታት ይከተለው የነበረው ‘ከፋፍለህ ግዛ’ ባዕድ ርዕዮተ ዓለም በነበረው የበታችነት አስተሳሰብ ምክንያት የተጠቀመበት ስልት እንደነበር አንስተዋል።
በዚህም ምክንያት በሕዝቦች መካከል መተማመን እንዳይኖር አድርጓል፤ ሕዝቦች በጠላትነት እንዲተያዩ መሥራቱን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ትህነግ በሠራው ግፍ እና በደል በኢትዮጵያ ሕዝብ ከአዲስ አበባ ከተባረረ በኋላም ብሔራዊ ስጋት ኾኖ መቀጠሉን አቶ ሽዓለሙ አንስተዋል። ለዚህ ደግሞ የሀገር ዘብ በሆነው መከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረገው ጥቃት ዋነኛው ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።
ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በኋላም በቅርቡ መንግሥት የሕዝቦችን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ ያደረገውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ በመጣስ በራያ፣ በጠለምት እና በአፋር አካባቢዎች እያካሄደ ያለው ትንኮሳ ሌላኛው ብሔራዊ ስጋት ኾኖ ቀጥሏል ብለዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ካለው ስትራቴጅክ አቀማመጥ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያን ዕድገት ከማይፈልጉ እና ቀጠናውን ለመቆጣጠር ከሚፈልጉ እንደ ግብጽ፣ ሱዳን እና ምዕራባውያን ጋር በመጣበቅ የለመደውን የባንዳነት ሥራ መቀጠሉም ሌላው የቡድኑ ሀገር ሻጭነት ማሳያ መሆኑን ነው የገለጹት።
በዚህም እንደ አሜሪካ የመሠሉ ሀገራት በሀገሪቱ ላይ እያደረጉት ያለው ያልተገባ ጣልቃ ገብነት በማሳያነት አንስተዋል። በዓለም አቀፍ አደባባይ የተለያዩ የሐሰት መረጃ በማሰራጨት የሀገርን ገጽታ እያበላሸ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
አቶ ሽዓለም በቀጣይ መንግሥት ቢከተላቸው ያሏቸውን ነጥቦችም አብራርተዋል።
ይህንን የጋራ ሀገር ስጋት የሆነውን አሸባሪ ቡድን ለማስወገድ ኢትዮጵያውያን የጋራ ትግል እንደሚጠበቅባቸው መክረዋል።
በሕግ ማስከበር ዘመቻው የተገኘውን ድል በቀጣይ በፓለቲካው፣ ዲፕሎማሲው እና በፕሮፖጋንዳው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ ሎቢስቶችን ጭምር በማቋቋም መሥራት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
አሸባሪው ትህነግ ለውጭ ሚዲያዎች የሚያሰራጫቸውን የተሳሳቱ መረጃዎች ተከታትሎ ምላሽ መሥጠት እንደሚገባም እንደ መፍትሔ አስቀምጠዋል።
በአሸባሪው ትህነግ የወጡ ለሀገር አንድነት ስጋት የሆኑ ሕጎችን ጭምር ማሻሻል እና እንደገና ማደራጀት እንደሚገባም አንስተዋል። ቡድኑ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እያወናበደ የሚገኘው በራሱ አምሳል የቀረጸውን ሕገ መንግሥት በመጠቀም ነው ብለዋል።
በየትኛውም መንገድ የሀሳብ ልዩነት ቢኖር በጋራ እና በአንድነት ሀገሪቱ የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ መከላከል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ማኅበረሰቡም ሠራዊቱን በሀሳብ፣ በቁሳቁስ እና በገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፣ አካባቢን ነቅቶ መጠበቅ እና የሚለቁ መረጃዎችን ምንጫቸውን መረዳት ይገበዋል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
