1ሺህ 442ኛው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በአዲስ አበባ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡

197

1ሺህ 442ኛው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በአዲስ አበባ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 442ኛው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በአዲስ አበባ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ስታዲዬም በተከወነው የኢድ ሶላት ሥነ ስርዓት ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሐጂ ሱልጣን አማን የዘንድሮው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የሚከበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኹለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት በተጠናቀቀበት ማግስት በመኾኑ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረ ገልጸዋል፡፡

ግድቡ እንዲጠናቀቅና ሕዝብን እንዲጠቅም ያላቸውን መልካም ምኞትም ገልጸዋል፡፡ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ሲከበር ለአላህ ትእዛዝና ለእስልምና ሲባል የሚከፈል የታዛዥነትና የመስዋእትነት ጥግን ለመዘከር የሚከበር መሆኑን ነው የገለጹት ሐጂ ሱልጣን፡፡ ከነብዩ ኢብራሂም አላህን መፍራትና ለትእዛዙ ተገዢ መሆንን መማር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በዓለም የሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በጋራ በመሆን የሐጂ ሥነ ስርዓት የሚፈጽሙበት በመሆኑ አንድነትን ያስተምራል ብለዋል ሐጂ ሱልጣን፡፡ አማኞቹ የሀገር ድንበር ሳይገድባቸው፣ የቆዳ ቀለም ሳይለያያቸው፣ የሀብት መጠን ሳይነጣጥላቸው፣ የስልጣን ደረጃ ሳይከፋፍላቸው፣ የአመለካከት ልዩነት ሳይገድባቸው፣ በአንድ ቦታ፣ በአንድ አይነት አለባበስ፣ በአንድ አይነት አምልኮታዊ ሥርዓት አንድ ፈጣሪያቸውን የሚያመልኩት በመሆኑ አንድነትን የሚያስተምር ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

“ስለ ዓለምና ስለ ዓለማቀፋዊ ወንድማማችነት ከሚሰብከው ዲናችን በላይ ምን ስለ ወንድማማችነት ማሳያ ይኖራል?” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ምእመኑ ልዩነትን ከሚፈጥር አስተሳሰብ መራቅ እንዳለበትም አስተምረዋል፡፡ ግንዛቤን ከጥፋት ይልቅ ለልማለት፣ ከጥበት ይልቅ ለስፋት፣ ከክፋት ይልቅ ለቀናነት ማዋል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በመልካም አስተሳሰብ የታነፀ ትውልድ ለዲኑም ሆነ ለሀገሩ መተኪያ የሌለው ሀብት ነውም ብለዋል፡፡

ዲኑ የረህመት፣ የመተዛዘን እንደሆነም ሐጂ ሱልጣን ገልጸዋል፡፡ የአላህ መልዕክተኛ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) “በምድር ላሉ ሁሉ እዘኑ፤ በሰማይ ያለው ያዝንላችኋል” ማለታቸውን አንስተዋል፡፡ የሃይማኖቱ ተከታዮችም እንደ ትእዛዙ ሊሆኑ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

ዛሬ የሚከናወነው እርድም አንድ ሶስተኛው ለምስኪን ወገኖች ማካፈሉን እንዳይረሳ ነው አደራ ያሉት፡፡ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ ጠንከር ብሎ በመሥራት ሀገርን ከድህነት ለማላቀቅ መረባረብ ይገባልም ብለዋል፡፡

ʺሰዎች ኾይ ሰላምን አንግቡ፣ ምስኪንን መግቡ፣ ዝምድናን ቀጥሉ፣ ሰዎች በተኙበት ለጌታችሁ ቁሙ፣ የጌታችሁ ጀነት በደኅንነት ግቡ” ተብሏልም ብለዋል ሐጂ ሱልጣን፡፡ የሚጎዱት እንዲርቁ የሚጠቅሙት እንዲቀርቡም ፕሬዝዳንቱ ተመኝተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article1 ሽህ 442ኛው የኢድ አል አደሃ አረፋ በዓል በደሴ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡
Next articleበጣና ሃይቅ ላይ ስትጓዝ የተሰወረችው ጀልባ ካፒቴን አስከሬን መገኘቱን የምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡