
“በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት የተራቡትን በማብላት እና በማጠጣት ኀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል” ሼህ ሰይድ ሙሐመድ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 442ኛው የኢድ አል አድሃ በዓል በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሁነቶች እየተከበረ ነው፡፡ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰይድ ሙሐመድ “በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተራቡትን በማብላት እና በማጠጣት ኀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል” ብለዋል፡፡ ሼህ ሰይድ ማንኛውም አቅም ያለው የእስልምና እምነት ተከታይ በሕይዎት ዘመኑ አንድ ጊዜ ሐጅ በሚፈጸምበት ቦታ በመሄድ የሐጅ ስርዓት መፈጸም እንዳለበት ከአምላክ የተሰጠ ትእዛዝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሼህ ሰይድ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል እስማኤል ለአባቱ ለኢብራሂም እና ለአምላኩ ለአላህ ታዛዥነቱን ያሳየበት በዓል ነው ብለዋል፡፡ በኢድ አል አድሃ በዓል የሃይማኖቱ ተከታዮች በየዓመቱ ዘር ቀለም ቋንቋ ሳይገድባቸው ከአራቱም የዓለም ጫፍ ተገናኝተው የሚያከብሩት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ሼህ ሰይድ ይህንን ታሳቢ በማድረግ በሀገራችን በተፈጠሩ ችግሮች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
“የዚህን ዓመት በዓል ስናከብር በርካታ ሀገራዊ ድሎችን ያስመዘገብንበት ዓመት በመሆኑ ደስታችን እጥፍ ነው፤ ይህ ደስታችን እንዲቀጥል ሁላችንም ኀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል” ነው ያሉት፡፡ ሼህ ሰይድ ሀገር ወደ ተሻለ ጉዞ እንድታቀና ሁሉም በገንዘብ በጉልበት እና በሀሳብ በማገዝ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በተለያየ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን በጸሎት ማሰብ እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
