
“ዛሬ የለውጥ ቀን ነው” ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ)1 ሽህ 442ኛ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ኹነቶች እየተከበረ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲዬም በተከናወነው የጋራ የኢድ ሶላት መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ “ዛሬ የለውጥ ቀን ነው” ብለዋል፡፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከመካ ወደ መዲና በገቡ ጊዜ የመዲና ሰዎች በዓመት ሁለት ጊዜ እየተሰባሰቡ የሚለያዩበት ሥርዓት ነበራቸው ነው ያሉት፡፡ ነብዩም በዚያ በገቡ ጊዜ የመዲና ሰዎች የሚያደርጉትን አዩ “የእናንተ ስብስብም ለዚህ ዓለም ብቻ ነው፤ እኔ ወደ ሚጠቅም ነገር ልለውጥላችሁ” አሏቸው፡፡ ነብዩም ወደ ኢድ አል አድሃ እና ወደ ኢድ አል ፈጥር ቀየሩላቸው ነው ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ፡፡
ጥሩ ልምድና ጥሩ ባሕል ያለው በዚው ይቀጥላል፤ መጥፎ ያለበት ግን በዚያው ተገትሮ ከመኖር ወደ መልካሙ ነገር መዞር ይሻላል ብለዋል፡፡
በኢድ አል ፈጥር ተበልቶ ሶላት ሲሰገድ በኢድ አል አድሃ ምግብ የሚበላው ከሶላት በኋላ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
በኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ሃይማኖቱ የሚፈቅደውን በጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባዔ ወይዘሮ ዘርፈሽዋል ንጉሤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖቱ ተከታዮች ተገኝተዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
