የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የኢድ አል አዳሃ አረፋ በዓልን ሲያከብሩ አቅመ ደካሞችን በመርዳት መሆን እንዳለበት የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ፡፡

221

የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የኢድ አል አዳሃ አረፋ በዓልን ሲያከብሩ አቅመ ደካሞችን በመርዳት መሆን እንዳለበት የሃይማኖት
አባቶች አሳሰቡ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 442ኛው የኢድ አል አዳሃ (አረፋ) በዓል እየተከበረ ይገኛል። በዓሉ ሲከበር
ማንኛውም የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ምን ማድረግ እንደሚጠበቅበት፣ በዓሉም በምን መልኩ መከበር እንዳለበት በባሕር ዳር
የሃይማኖት አባቶችን አነጋግረናል።
የኢድ አል አድሃ (አረፋ)በዓል በእስልምና ሃይማኖት ታላቅ ቦታ የሚሰጠውና በታላቅ ደስታ፣ በጸሎት የሚከበር፣ ሸሪዓ
በሚፈቅደው መሰረት በጨዋታ የሚከበርበት ቀን እንደሆነ የሰላም በር መስጅድ የዳዕዋ ዘርፍ ኀላፊ ዶክተር ሼህ መሐመድ ከማል
አስረድተዋል።
“አላህ ነብዩ ኢብራሒምን ልጁን እንዲሰዋለት ጠየቀው። ነቢዩ ኢብራሒምም ጥያቄዉን በደስታ ተቀብሎ ልጁ ኢስማኤልን ለአላህ
ሊሰዋው እንደሚፈልግ ይነግረዋል። ኢስማኤልም በደስታ ተቀብሎ ታዛዥ መሆኑን ገልፆለታል። አላህ ይህን የኢብራሒምን
ታዛዥነት አይቶ ልጁን ከመሰዋቱ በፊት ሙክት አቅርቦለት እንዲታረድ አደረገ” ብለዋል።
ሼህ መሐመድ የአሁኑ ትውልድም ትዕዛዝን መቀበልና ማክበር ተገቢ እንደኾነ ከዚህ ትምህርት መውሰድ አለበት ነው ያሉት።
አላዳሃ ማለት ረፋድ ላይ የሚከናወን የጸሎትና የደስታ፣ ሸሪዓ በሚያዘው መሰረት የሚተገበር የኢባዳ አይነት መሆኑን
ገልጸውልናል።
“አረፋ ማለት ደግሞ ከመካ 20 ኪሎሜትር ርቃ የምትገኝ ቦታ ናት። በመሆኑም ወሩ በገባ (ዙልሂጃ) በገባ በ9ኛው ቀን ሐጅ
ግዴታ የሆነበት ግለሰብ ኹሉ በዚህ ቦታ ላይ መቆም ግዴታው ነው” ብለዋል። ይህም መካ አረፋ በመባል እንደሚታወቅ ሼህ
መሐመድ አስረድተዋል። በዚያኑ ቀን በቀሪው ዓለም የሚኖሩ ሙስሊሞች ጾመው ይውላሉ፣ የሁለት ዓመት ሐጢዓት (ወንጀል)
ያሰርዛል ተብሎ ይታመናል ነው ያሉት።
ኢድ አል አድሃ (አረፋ) በሚከበርበት ቀን ጠዋት ከተሰገደ በኋላ ጤንነቱ ያልተጓደለ፣ ሙሉ የኾነ እንስሳ የሚታረድበት ቀን
መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለእርድ የሚፈቀዱትም በግ፣ ፍየል፣ ከብትና እንደሆኑም ጠቅሰዋል።
በዓሉን ለማክበር እርድ የሚፈጽም ማንኛውም የሃይማኖቱ ተከታይ ሲሶዉን ለአቅመ ደካሞች እንዲሰጥ ሃይማኖቱ
እንደሚያስገድደው አስረድተዋል።
“ዛሬ የአላህ እንግዶች ስለኾናችሁ ስገዱ፣ ብሉ ጠጡ ተደሰቱ አላህን ዝከሩ እንጂ እንዳትፆሙ” ተብሎ መታወጁን ተናግረዋል።
በኢድ አልአድሃ አረፋ በዓል ከስግደት መልስ እርድ ከተፈጸመ በኋላ መጀመሪያ ጉበቱ ነው መበላት ያለበት ብለዋል። ይህም
የሚሆነው በጀነት የአላህ መስተንግዶ የሚጀምረው ጉበትን በመቋደስ መሆኑን አስረድተዋል።
ሙስሊሙ ከስግደት ሲመለስ ኢፍጣሩ መኾን ያለበት በጉበት ነው ብለዋል። ከእርድ በኋላ ቆዳው ለተለያየ አገልግሎት ይውላል
ወይም ሰደቃ ይደረጋል እንጂ እንዳይሸጥ ሃይማኖቱ ይከለክላል ነው ያሉት።
በዓሉን አስመልክቶ ኢድ ከሚከበርበት ቀን ጀምሮ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ እርድ መፈጸም እንደሚቻልና ይህም ማታ ሳይሆን
ቀን መሆን እንደለበት አስረድተዋል።
የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ሲከበር ዘመድም ኾነ ሌሎች ድሆች በምንም አይነት መረሳት የለባቸውም ያሉት ደግሞ የቶፊቅ
መስጅድ ኢማም ሼህ ጀዋር መሐመድ ናቸው። “እኛ ብቻ ሳንኾን ሁሉንም ወገን ማስደሰት ይኖርብናል” ብለዋል።
በአረፋ በዓል ዘመድ አዝማድ የሚጠያየቅበት ከሩቅና ከሀገር ውጪ እንኳን ቢሆን በተለያዩ መገናኛዎች መጠያየቅ የበዓሉ
መገለጫ እንደኾነ ጠቁመዋል።
በበዓሉ ቀን የሃይማኖቱ ተከታዮች ሰዉነታቸዉን በመታጠብ፣ ጥርሳቸውን በመፋቅ፣ ሽቶ በመቀባት፣ የሚያምረውን ወይም የታጠበ
ልብስ በመልበስ ራሳቸውን ለደስታ ዝግጁ ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
በዕለቱ የታመሙትን ወገኖች መጠየቅ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን እንዴት እያከበራቸሁ ነው?
Next article“ዛሬ የለውጥ ቀን ነው” ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ