
የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን እንዴት እያከበራቸሁ ነው?
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በተለይ የሚከወነው የመረዳዳት እሴት በሌሎች ቀናትም ሊቀጥል እንደሚገባ ነው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከተለያዩ አካባቢዎች በስልክ ያነጋገራቸው የሃይማኖቱ ተከታዮች የገለጹት፡፡
ኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡ በዓሉ እርድና የመረዳዳት በዓል ተብሎ ይታወቃል፡፡
የእርድ በዓል የተባለበት ምክንያትም ነብዩ ኢብራሒም (ዐ.ሰ) የአምላካቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም ሲሉ ልጃቸውን ለመሰዋት ያዘጋጁበት ቀን በመሆኑ ነው፡፡ እናም ዛሬ በዓሉ ለ1ሺህ 442ኛ ጊዜ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡
በዓሉን በሃማኖታዊ አስተምህሮቱ መሠረት እያከበሩ መሆኑን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከተለያዩ አካባቢዎች በስልክ ያነጋገራቸው የሃይማኖቱ ተከታዮች ተናግረዋል፡፡
የቡሬ ከተማ ነዋሪው አቶ አብዱ ደጉብርሃን እንደነገሩን በዓሉ የእርድ በዓል እንደመሆኑ ማንኛውም የእምነቱ ተከታይ ለቤቱ ያዘጋጀውን እርድ ለሦስት በመክፈል አንዱን እጅ ለምስኪኖች እና ለጦም አዳሪዎች እንዲሠጥ፤ አንዱን እጅ ቤቱ በማዘጋጀት ጎረቤቶችን እና ወዳጅ ዘመዶችን እንዲጋብዝ፤ አንዱን እጅ ከቤተሰቡ ጋር እንዲጠቀም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አዝዘዋል፡፡
አቶ አብዱ በዓሉ እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንደሚከበርም ነግረውናል፡፡ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ሲከበር ሌሎች ተደስተው ሲዉሉ ምስኪኖች እና ጦም አዳሪዎች አዝነውና ተክዘው እንዳይውሉ በማሰብ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የሠሩት ሥርዓት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
አቶ አብዱ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የእርድ ሥነ ስርዓቱ የሚፈጸመው የኢድ ሶላት ከተሰገደ በኋላ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ነብዩ ኢብራሒም (ዐ.ሰ) የአምላካቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም ልጃቸውን ለመስዋእትነት እንዳቀረቡ ሁሉ ሌሎችም ፈጣሪያቸውን ለማስደሰት ትዕዛዙን በአግባቡ እየተገበሩት ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ወቅት ሚስተዋለው መደጋገፍ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የሚከናወን ተግባር ሊሆን እንደሚገባም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የደካሞችን ቤት በማደስ፣ ለጦም አዳሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን በማቅረብ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ባይ ናቸው፡፡
ማኅበረሰቡ በበዓል ወቅት ከመረዳዳት ባሻገር ሀገራዊ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በጋራ መቆም እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ጃዊ ወረዳ ፈንድቃ 02 ቀበሌ ነዋሪው አቶ ሰማኸኝ ፈንታሁን በመላው ዓለም ለ1ሺህ 442ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሁሉም አቅጣጫ መደጋገፍን የሚጠይቅ ወቅት ነው ብለዋል፡፡ በዓሉ የመረዳዳት በዓል በመሆኑ ያለው ለሌለው ያካፍልበታል፤ ያግዝበታል፤ የፈጣሪውን ትዕዛዝ ይፈጽምበታል ብለዋል፡፡
አቶ ሰማኸኝ በዓሉን በጋራ ከማክበር በተጨማሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የሚደረገውን ንቁ ተሳትፎ እንዲጎለብት ይረዳል ነው ያሉት፡፡
አቶ ሰማኸኝ የኑሮ ውድነቱ እያሸቀበ መሆኑን ጠቅሰው ብዙዎች ለችግር እንዳይዳረጉ መረዳዳቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የደሴ ከተማ የእስልምና ጉዳይ ሕዝባዊ መጅሊስ ሊቀመንበር ሼህ እድሪስ በሽር አደም ወቅቱ መረዳዳትን የሚጠይቅ በመሆኑ ተግባራዊ እያደረግነው ነው ብለዋል፡፡ ሼህ እድሪስ እንዳሉት አረፋ በአል ድሃውም ሀብታሙም በእኩል ተደስተው የሚያከብሩት በዓል ነው፡፡ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ባስተላለፉት መልዕክት ማንኛውም የእምነቱ ተከታይ አቅሙ በፈቀደ ያዘጋጀውን የበዓል መዋያ እርድ በታዘዘው መሰረት ማካፈል ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
ሼህ እንድሪስ ከበዓሉ ባሻገር ወቅቱ ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ መረዳዳት የሚያስፈልግበት በመሆኑ የተለያዩ ድጋፎች ለተፈናቃዮችና ችግር ለደረሰባቸው ሰዎች እንዲደርስ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወቅቱ መረዳዳትን የሚጠይቅ ነው፤ ይህንንም በአግባቡ መፈጸም ተገቢ ነው ብለዋል ሼህ እድሪስ፡፡ ከመረዳዳቱ ባሻገር ሁሉም በየ ሃይማኖቱ ጸሎት ማድረግ ተገቢ መሆኑን በመግለጽ፡፡
ሼህ እድሪስ በደሴ ከተማ በጎ አድራጎት ሥራን አጠናክሮ በመቀጠል የመረዳዳት እሴቱ ዘላቂ እንዲሆን እየሠሩ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ ስጦታን በዓልን ብቻ ጠብቆ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ መሥጠት ግድ እንደሚልም ነው የገለጹት፡፡ ሼህ እንድሪስ “ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት መደጋገፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” ብለዋል፡፡
መልካም በዓል!
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
