
“እኛ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን የማንሻገረው ችግር የለም” የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 12/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ ሁለተኛው የውኃ ሙሌት መጠናቀቁ ከተነገረ በኋላ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ ለአሚኮ እንደገለጹት ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ሕዝቡ ድጋፍ ማድረጉን መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
አቶ ቢንያም አክሊሉ የግድቡ ሁለተኛው የውኃ ሙሌት መጠናቀቅ ማንነታችንን በድል የመገንባት ያክል ይቆጠራል ነው ያሉት። በበሳል አመራርነት፣ በትዕግስትና በትግል የተገኘ ውጤት ነው ብለዋል። ወደፊትም ቢሆን በሀገሪቱ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ኅብረተሰቡ በገንዘብ፣ በዕውቀት እና በጉልበት መደገፍ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

“ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው የውኃ ሙሌት መጠናቀቁ ሀገሪቱ ወደተሻለ ከፍታ ላይ እየተጓዘች መሆኑን ያመላክታል” ያለችው ደግሞ ተማሪ እየሩስ ጥላሁን ነች።
በውጪ ጣልቃ ገብነት ምክንያት የግድቡ ውኃ ሙሌት መካሄድ አስግቷት እንደነበርና ዛሬ ግን የግድብ 2ኛው የውኃ ሙሌት መጠናቀቁ ዜና ስትሰማ ደስታዋን መቆጣጠር እንደተሳናት ገልጻለች።
ኢትዮጵያውያን ለኹሉም የልማት ሥራዎች ተባብረን መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያለችው።
ፋንታሁን ሙጬ የተባሉት ነዋሪ ደግሞ ከኃይል ማመንጨት ጀምሮ ባለ ብዙ ተስፋ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው የውኃ ሙሌት መጠናቀቁ ለሀገሪቱ ሕዝቦች ሁለንተናዊ ድል ነው ብለዋል። “በሀገራችን የሚስተዋለው የሰላም ችግር ለጊዜው መስዋዕትነት ያስከትላል እንጂ ሰላም መፈጠሩና ዕድገት ማስመዝገባችን አይቀርም” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ቀሪ እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶችም የኛው ስለሆኑ በጋራ ልናጠናቅቃቸው ይገባል ነው ያሉት።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ወጋየሁ ዘሪሁን የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴግድብ ሁለተኛው የውኃ ሙሌት መጠቀቅ ኢትዮጵያውያን አንድ ከሆኑ ሁሉንም ችግሮች ማለፍ እንደሚቻል ያሳያል ብለዋል። “እኛ ኢትዮጵያውያን የሚገጥመንን የውስጥም ሆነ የውጪ ጠላትን በመቋቋም ከተባበርን የማንሻገረው ችግር የለም” ነው ያሉት ነዋሪው።
በአንድ ዓላማ ኾኖ እየተገነቡ የሚገኙትንም ሆነ ወደፊት የሚገነቡ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
 
             
  
		