ለህልውና ትግሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ፡፡

171
ለህልውና ትግሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ፡፡
ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2013 ዓ.ም(አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ቡድን ጥቅምት 24 የሀገር ደጀንና ከለላ በኾነው መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም ሀገርን ሲያዋርድ እና ዳግም ክህደት ሲፈጽም ቀድሞ ደርሶ ክንዱ የኾነው የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ቡድኑን እንዲንኮታኮትና ከመሸገበት መቀሌ ወርዶ ጉድጓድ እንዲገባ ጀብዱ ፈጽሟል፡፡
አማራ ክልል የተሰነዘረበትን ጥቃት ለመመከት እና ሕግ ለማስከበር በተሠራው ሥራ ከፍተኛ ወጭ አውጥቷል፡፡ ተተኳሽ ከማቅረብ እስከ ህክምና ቁሳቁስ፤ ከሠራዊት ሬሽን አቅርቦት እስከ መሰረተ ልማት ጥገናና ሌሎችም ወጭዎች በክልሉ መንግሥት ትከሻ ላይ የወደቁ ነበሩ፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ለዳግም ጥፋት መነሳቱን ተከትሎ ምላሽ ለመስጠትና የተጀመረውን የህልውና ዘመቻ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቋጨት የፌዴራልና የዲያስፖራውን ተሳትፎ ሳይጨምር በክልሉ ብቻ 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እየተሠራ መኾኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር ) ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
የህልውና ዘመቻውን ሁሉም እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አሁን እየታየ ያለው መደጋገፍ እጅግ የሚያበረታታ እንደኾነም ዶክተር ሙሉነሽ ገልጸዋል፡፡
ጉዳዮ የጋራ እንደኾነ ያስረዱት ዶክተር ሙሉነሽ ሁሉም በጋራ ሲቆም ችግሩን መፍታት ይቻላል ብለዋል፡፡ የውስጥና የውጭን ጠላት ለማሸነፍ መሠረቱ በጋራ መቆም እንደኾነም ነው የተናገሩት፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀብትም ይሁን በሙያ ሊደግፍ እንደሚገባ ነው ያብራሩት፡፡
የዲያስፖራው ማኅበረሰብም በሚችለው ሁሉ ሊያግዝ ይገባል ብለዋል፡፡ የተጀመረውን የህልውና ዘመቻ በድል ለመሻገር አብሮ መቆም በተግባር የሚፈተንበት ጊዜ እንደኾነም ነው የተናገሩት፡፡ ጊዜው በግለሰብ ደረጃ ያለው ቁርጠኝነትና ሀገር ወዳድነት የሚታይበት ነውም ነው ያሉ፡፡
እንደ አማራ ክልል በሕግ ማስከበር ሂደቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ለመዘርጋት እና ሌሎች መሠራት ያለባቸው ሥራዎች መኖራቸውን የተናገሩት ዶክተር ሙሉነሽ ለአጭር ጊዜ የሚኾን ድጋፍ ክልሉ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ ለዚህም 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ሀብት የማሰባሰብ ሥራ እንደተጀመረ ገልጸዋል፡፡
ከረጅም ጊዜ አኳያ ግን ከዚህ በላይ ሀብት ለማሰባሰብ እቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉ ሁሉም በሚችለው አቅም የበኩሉን ድጋፍ ካደረገ የሀብት ማሰባሰብ ሥራው ግቡን እንደሚመታ ዶክተር ሙሉነሽ ጠቁመዋል፡፡
የጥረት ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚና በአዲስ አበባና በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመው የድጋፍ ኮሚቴ አባል
ባምላኩ አስረስ (ዶክተር) የህልውና ዘመቻውን በድል ለመወጣት ከንግዱ ማኅበረሰብ ድጋፍ እያሰባሰቡ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡
የተገኙ ደረቅ ምግቦችን ከመሀል ሀገር ወደ ግንባር እያጓጓዙ መኾኑን ያስረዱት ዶክተር አምላኩ ከአሁን በፊት ለአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ድጋፍ ለመሰብሰብ ቃል የተገባውን ገንዘብ ለማሰባሰብ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን የገጠመን የህልውና አደጋ የአማራ ክልል ብቻውን የሚወጣው ሳይኾን የሀገር ጉዳይም እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት፡፡
ሁሉም ዜጋ በሚችለው ሁሉ ሊደግፍ ይገባል ያሉት ዶክተር ባምላኩ በአሁኑ ወቅት አማራ ክልል ተጎራባች በመኾኑና ቀጥተኛ ጥቃትም በሕዝቦቹ ላይ በመታወጁ ግንባር ቀደም ሚና ይውሰድ እንጅ የሽብር ቡድኑ ሀገራዊ የህልውና አደጋ በመኾኑ በግንባር ከመሰለፍ እስከ ቁሳቁስ ድጋፍ ሁሉም እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
4 ኪሎ በሚገኘው የክልሉ ኢንቨስትመንት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በመገኘት በፌዴራል ደረጃ ለተቋቋመው የድጋፍ ኮሚቴ ድጋፍ ለሚሰጡ ሁሉ ዝግጁ ሆኖ የሚጠብቅ መኾኑን ዶክተር ባምላኩ ጠቁመዋል፡፡ በተዘጋጁ የባንክ ቁጥሮችም መለገስ እንዲቻል አማራጮች መቀመጣቸውን አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ:- ጋሻው ፈንታሁን -ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የኢትዮጵያዊያን ልዩ የድል ብስራት ቀን ነው” ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ
Next articleየኢድ አል አድሃ አረፋ በዓልን ስናከብር ሕዝበ ሙስሊሙ ለተቸገሩ እዝነት በማድረግ ሊሆን እንደሚገባ የጎንደር ታላቁ መስጊድ አስተዳዳሪ አሳሰቡ።