የወልቃይት ሕዝብ የጀግና እግርን ያጥባል፤ ባንዳን ደግሞ ይመነጥራል፡፡

167
የወልቃይት ሕዝብ የጀግና እግርን ያጥባል፤ ባንዳን ደግሞ ይመነጥራል፡፡
ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2013 ዓ.ም(አሚኮ) ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ትህትናውን ገልጿል። በወገኖቹ ዘንድ ፍቅሩን ለማጽናት እግር አጥቧል፤ በማበሻ ጨርቅም አብሶላቸዋል፡፡ ይህንን ያደረገው ያለውን ጥልቅ ፍቅር ለመግለጽና በሕይወታቸው ሲተገብሩት ማየት የሚፈልገውን ባሕርይ በምሳሌነት ለማስተማር ነው፡፡ መምህር ኾኖ የተማሪዎቹን እግር ማጠቡ፣ የፍጡራን ጌታ ሎሌዎቹን ማገልገሉ ለሰው ልጅ ትሕትናን ሊያስተምር፣ ፍቅርን ሊሰብክ፣ ምህረትን፣ ርህራሄን፣ ቸርነትን፣ መዋደድን፣ የዋህነትን እና ትዕግሥትን በወዳጆቹ ዘንድ ሊያኖር ነው። ከአጠበ በኋላም “እናንተም እርስ በርሳችሁ እንዲሁ ታደርጉ ዘንድ ይገባችኋል” ብሎ አስተምሯል፡፡
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን የሑመራ ከተማ ወጣቶች ከፈጣሪያቸው የተሰጣቸውን ተግብረዋል፡፡ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለፌዴራል ፖሊስና ለአማራ ክልል ልዩ ኀይል ያላቸውን ክብርና አድናቆት ለመግለጽ እግር አጥበዋል።
የሑመራ ነዋሪዎች ድሮም ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው፣ ወገን ወዳድ፣ ለክብራቸው ሟች፣ ለኢትዮጵያዊ ዕሴታቸው፣ ለወግና ባሕላቸው፣ ለእምነታቸው እንዲሁም ለማንነታቸው አብዝተው የሚጨነቁ ናቸው። በክፋት ካልሄዱባቸው በስተቀር ቤታቸውም ልባቸውም ለፍቅር ተዘግቶ አያድርም። እንግዳ ተቀብሎ ማስተናገድ ያውቁበታል። ቤት ለእንቦሳ ብሎ ለዘለቀ ቤታቸው ያፈራውን ጋብዘው አልጋቸውን ለቅቀው ያስተኛሉ፡፡ ማብላትና ማጠጣት የተለመደ ነው፤ እግር ማጠብ ደግሞ ትልቅ ክብራቸው ነው። ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው የወረሱት መልካም ስብዕናቸው ነውና።
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ግን እምነት አልባ ትውልድ ፈጥሮ የጥፋት ደቀመዛሙርት አፍርቷል፡፡ የሱን ፈለግ የተከተለ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ዕሴቱን፣ ባሕሉን፣ የማንነት መገለጫውን ዘንግቷል። ክብሩንና ብኩርናውን አሳልፎ ሰጥቷል። ባዕድ ማንነትን ተጣብቶ ከወገኑ ጋር ተጋጭቷል። እምነት ቢሰጥም አልታመን ብሎ ሀገርና ሕዝብን በድሏል። ከፍቅር ይልቅ ጠብ አጫሪነትን መርጧል። ከሰብዓዊነት ይልቅ ገንዘብን አስቀድሟል፡፡ ይህ የአሸባሪዎች ቡድን ተነግሮ የማያልቅ ግፍና በደል አድርሶ ክብሩን በራሱ ጊዜ አጥቷልና ከመሪነት ወደ አሸባሪነት ተንኮታኩቷል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አማራዎች በሂደቱ ብዙ ጀግኖችን፣ በርካታ ንጹሃንን ቢገብሩም በማንነታቸው የመጣባቸውን ዳግም ላይመለስ ቀብረውታል፡፡
በክፋት ለሄደባቸው ግን ምሕረት አያውቁም፡፡ እስከመጨረሻው ይፋለማሉ እንጂ፡፡ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ከአሸባሪው ትህነግ ጋር ያደረጉት እልህ አስጨራሽ ፍልሚያና ያገኙት አንጸባራቂ ድል ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ለዘመናት ያጣውን ፍቅር፣ ትህትና፣ ክብርና ደስታ አሁን ያለ ስስት ሰጥቶ መቀበል ጀምሯል። ለ41 ዓመታት በዘለቀ እልህ አስጨራሽ ትግሉ ነጻነቱን አግኝቷል፤ ለዓመታት ማዕቀብ የተጣለበት የአማርኛ ሙዚቃ በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች በነጻነት መደመጥ ጀምሯል፤ ያስገድል የነበረው ፉከራና ቀረርቶ አሁን የነዋሪዎቹ ድምቀት ኾኗል፡፡
የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን በተንቀሳቀሰባቸው ማይካድራ፣ ሑመራ፣ ቃብትያ፣ በአከር፣ እና ዳንሻ ከተሞች የነዋሪዎች ነጻነት፣ ፍቅርና አንድነት እጅግ የሚያስቀና ነው፡፡ ይህ ደስታቸው ግን ለዓመታት ርቋቸው ነበር፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሰዎች ሀገራቸውን አብዝተው ይወዳሉ፤ አጥንታቸው ቢከሰከስ፣ ስጋቸው ቢቆረስ፣ ደማቸውም ቢፈሰስ ማንነታቸው ኢትዮጵያዊነት፣ ዝቅ ካለም አማራነት ነው፡፡ ኢትዮጵያን በክፉ ለሚያይ፣ በከንቱም ሊያፈርሳት ለሚሻ ትዕግስት የላቸውም፤ እንደለመዱት ጎራዴያቸውን ስለው፣ ጠመንጃቸውን ወልውለው ፍልሚያ ይገጥማሉ፡፡ በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ የወልቃይት ሰዎች ያደረጉት ተጋድሎም ሕያው ኾኖ የሚነገር አኩሪ ታሪክ ነው፡፡
ለሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንም የተለዬ ፍቅር አላቸው፡፡ ስለ ሀገር እየተዋደቁ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለአማራ ልዩ ኀይልና ለሚሊሻው ልዩ ክብር ሰጥተዋል፤ በትግላቸው ሁሉ አብረው ናቸው፡፡ ደጀን ሕዝብ ስለኾኑ ወደፊትም ጥሩ የሠሩትን እያመሰገኑ፣ እግር እያጠቡ አብረው ይዘልቃሉ፡፡ ለሚተነኩሳቸው ደግሞ መልስ መስጠቱን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ነዋሪዎች ያውቁበታል፡፡
ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ-ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleʺኢትዮጵያ ያለችውን አሳክታለች፣ የተባለላትን አምክናለች”
Next articleፕሬዘዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለኢድ አል አድሐ ( አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡