ʺኢትዮጵያ ያለችውን አሳክታለች፣ የተባለላትን አምክናለች”

165
ʺኢትዮጵያ ያለችውን አሳክታለች፣ የተባለላትን አምክናለች”
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 12/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን የሚጠብቃት ኃያል አምላክ እንጂ፣ የሚያጠቃት ኃይል ሀገርና መንግሥት የለም፡፡ አይበገሬ፣ አይደፈሬ ናትና፡፡ የሚንቋት ይዋረዳሉ፣ የሚያከብሯት ይከብራሉ፣ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም እያሸነፈች፣ መከራውን እያለፈች፣ የማለዳ ብርሃን እየፈነጠቀች፣ የማዕቱን ወንዝ እየተሻገረች አዲስ ዘመን፣ አዲስ ስልጣኔ ታያለች፡፡ ጠላቶቿ ሁሉ ይጠፋሉ፣ ወዳጆቿ ሁሉም ይበዛሉ፣ በክፉ የሚያስቧት የሚናገሩበት ልሳን፣ የሚሻገሩበት መንገድ ይዘጋል፡፡ አጨለምንባቸው ያሉት ዘመን ይነጋል፡፡
ከሁሉም፣ በሁሉም የቀደመችው ሀገር ኢትዮጵያ ትጸናለች፣ ጸንታም ታጸናለች፡፡ በክፉ የመጣውን ቀጥታ ትመልሳለች፣ በመልካም የመጣውን አቅፋ ትቀበላለች፣ አሞናሙና ታስተናግዳለች፣ አስደስታ ትሸኛለች፡፡ ክብሬን አታሳንሱ፣ ድንበሬን አታፍርሱ፣ መልካም ስሜን አታርክሱ ትላለች ኢትዮጵያ፡፡ በክብሬና በድንበሬ የመጣ ሁሉ የፈረጠመውን ክንዴን ይቀምሳል፣ እድለኛ ከሆነ በመጣበት እግሩ ይመለሳል፣ ካለበለዚያ ግን በበትሯ ወድቆ አፈር ይልሳል፡፡
ዘመናትን እየጠበቁ ኢትዮጵያ ደከመች ብለው ባሰቡ ቁጥር ሊያጠቋት የሚቀምጡት ብዙዎች ናቸው፡፡ የደከመች በመሰላቸው ጊዜ ከሚደግፏት የሚነቅፏት፣ ከሚያከብሯት በንቀት የሚመለከቷት፣ በመልካም ከሚያነሷት በክፉ የሚያነሷት ይበዛሉ፡፡ ከደከመች የበለጠ እናድክማት፣ ከተናጋች የበለጠ እናናጋት እንጂ ከደከመች እናጠንክራት፣ ካጎነበሰች እናቃናት የሚላት የለም፡፡ በእርግጥ እንደ ጠላቶቿ አይብዙ እንጂ በመከራዋ ቀን ከጎኗ የሚሰለፉ፣ የችግሩን ቀን አብረው የሚያልፉ ወዳጆችም አሏት፡፡
ምድርን ያሳመረች፣ የሰውን ልጅ ያሰለጠነች፣ ዘመንን የዋጄች፣ ምስጢራትን ያመሰጤረች፣ ጥበባትን የተጠበበች፣ ፍጥረታትን በጥበብ የመረመረች፣ ሰማያትን ያሰሰች፣ ውቅያኖስን፣ በምድር ሽንቁር ውስጥ ሁሉ ያለውን ምስጢር ሁሉ አስቀድማ ያወቀች፣ ተከታዩች እንዲያውቁ፣ በጥበብ መንገድ እንዲራቀቁ ሲሻት በድንጋይ ላይ፣ ሲሻት በብራና ላይ ቀርጻ ያስቀመጠች፤ ዓለም ከተፈጠረ፣ ዘመን ከተቆጠረ፣ ጀምሮ ያለውን ታሪክ የምትዘክር፣ ከዓለም በፊት ምን ነበር ብላ የምትመረምር፣ ከዚህ ዘመን በኋላ ምን ሊመጣ እንደሚችል መስመር የምታሰምር፣ ጥበብን የታደለች፣ የጥበብን አምላክ ያከበረች፣ በጥበብ አምላክ የተከበረችና የተጠበቀች ናት ኢትዮጵያ፡፡
ጥበብንና ባለቤቱን ይዛለችና ልሥራ ብላ ካሰበችው፣ ላድርግ ብላ ካቀደችው፣ ልጓዝበት ብላ ከጠረገችው መንገድ የሚያግዳት የለም፡፡ ያለችውን ትፈጽማለች፣ ቃል የገባችውን ታጸናለች፣ ላድርግ ያለችውን አድርጋ ታሳያለች፡፡
እርሷ በስልጣኔ ጎዳና እየተጓዘች፣ አያሌ ስልጣኔዎችን እያሳዬች፣ ከስልጣኔ ርቀው በጨለማ ውስጥ የነበሩትን እያሰለጠነች በነበረችበት ዘመን መንግሥት ያላቋቋሙት፣ ሥርዓት ያልዘረጉት፣ ንጉሥ ያልሾሙት፣ መተዳደሪያ ያላበጁት፣ የሀገራቸውን ስያሜ ያላወጡት ዛሬ ላይ ዘመን ሰጥቷቸው፣ እርሷ ያሳዬቻቸው ጥበብ ተዘንግቷቸው ኢትዮጵያ ሆይ እኛን ስሚ ይሏት ጀምረዋል፡፡ እርሷም ታላቅ ታናናሾችን አስቀድሞ ይመክራል እንጂ፣ አይገስጽም፣ አይቀጣምና ተው የእኔ አካሄድ ከእናንተ ዘመን በእጅጉ ይርቃልና ባልኖራችሁበት ዘመን፣ በማታውቁት መንገድ ጣልቃ አትግቡ፣ በሉዓላዊነት፣ በአንድነትና፣ በክብር የልጆቼን እንጂ የእናንተን አልሰማም፣ ያላችሁኝንም አልፈጽምም፤ ይህስ በታሪኬም ተደርጎ አያውቅም ትላቸዋለች፡፡
ሉዓላዊነቴን አትንኩ ያለችው ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ድል እያደረገች የድል ችቦ ከተራራው ጫፍ ላይ ታበራለች፣ የተከበረውን ምድሯን ታስከብራለች፣ ከፍ ያለውን ታሪኳን በከፍታው ታዘልቃለች፡፡ የኢትዮጵያን ሥም ጠርተው፣ ሰንደቋን እያውለበለቡ የገሰገሱ ሁሉ ያለ ድል የተመለሱበት ጊዜ የለም፡፡ ቢሻቸው በሰላም ውድድር፣ ቢሻቸው በጦር ሜዳ ፉክክር ድል እያደረጉ ከሁሉም አስበልጠው ከፍ ያድርጋሉ፡፡
ዘመን ዘመንን ተክቶ፣ ታሪክ ለባለታሪኮች ሜዳውን አዘጋጅቶ፣ የታሪክ መሥሪያውን ቀለምና ድር ሰጥቶ አልፏል፡፡ ልጆቹም የማይሻነፍ ታሪክ ወርሰዋል፣ የታሪክ መሥሪያውን ሜዳ ተረክበዋል፣ ቀለምና ድሩን በእጃቸው ጨብጠዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሌላ ታሪክ እየሠሩ ነው፡፡ የዚሕ ዘመን ኃያላን ነን የሚሉት ኢትዮጵያን በሚቻላቸው ሁሉ ሊገፏት ከጀሉ፡፡ እርሷ ግን የሚገፋኝ ያጠነክረኛል፣ የሚንቀኝ ያከብረኛል፣ የሚጠላኝ ይወደኛል፣ መሸነፌን የሚመኝ ድሌን ያያል አለቻቸው፡፡
በዚሕ ዘመን ዓለም ኢትዮጵያን ከሚገፋበት አንደኛው የዓባይ ግድብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን እንገድባለን፣ ሌሎች ደግሞ ቢቻል እናፈርሰዋለን፣ ካልተቻለ ግን እናስቆመዋለን እያሉ ይዝቱባቸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊያን ግን አታፈርሱትም፣ አታስቆሙትም፣ ሁሉም ከእናንተ ሀሳብ በላይ ነው አሏቸው፡፡ ዓለማት በድንፋታ አስፈራሩ፣ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በዝምታ ሠሩ፡፡ በዝምታቸው የሠሩትንም ከፍ ባለ ድምጽ አበሠሩ፡፡ “እንሰራዋለን ያልነውን ሠራነው፣ እናደርገዋለን ያልነውን አደረግነው፣ ኢትዮጵያ አይደለም በጩኸት በጦርነት የማትደነግጥ ሀገር ናት” አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ያለችውን አሳክታለች፣ የተባለላትን አምክናለች፡፡ እነሆ ዛሬም አዲስ ታሪክ ሠርታለች፣ አዲስ ብሥራት አሳይታለች፡፡
አይሆንም አይደረግም ያሉት ሆኖ ተደርጎ አይተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ድሉን ከፍ አድርገው አብስረዋል፡፡ በጋራ እንደሠሩት በጋራ ተደስተዋል፡፡ ዓባይ ወንዛቸው ብቻ ሳይሆን ደማቸው፣ የሚሰባሰቡበት የጋራ ጎጇቸው፣ በጋራ የሚያቀርቡት በጋራ የሚቋደሱት የጋራ ማዕዳቸው መሆኑን አስመስክረዋል፡፡
ዓባይ ማደሪያውን ቀልሷል፣ በረሃውን አረስርሷል፣ ወንዝ ሆኖ ሳለ ሐይቅ ሆኗል፡፡ የራስ አለማስነካት፣ የሰውንም አለመንካት ይሕ ነው፡፡ በራስ፣ ለራስ፣ ስለ ራስ መኩራትም እንዲህ ነው፡፡ እርሷን የሚያቆማትም፣ የሚጠብቃትም ኃያል አምለኳ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ሁሉ ከእርሷ በታች ናቸው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ሁለተኛው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት በመጠናቀቁ እንኳን ደስ ያለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየወልቃይት ሕዝብ የጀግና እግርን ያጥባል፤ ባንዳን ደግሞ ይመነጥራል፡፡