
ʺኢትዮጵያን በየትኛውም አቅጣጫ የሚዳፈሩ እና የውጪ አካላት ፍላጎት አስፈፃሚ የሆኑ ኃይሎች ዳግም እንዳይመለሱ ሕዝቡ ተባብሮ ኃያልነቱን ማረጋገጥ አለበት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሊት አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ደመቀ ያስተላለፉት መልዕክት ቀርቧል።
ለመላው የሀገራችን ሕዝብ!
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሊት መርኃግብር በተሳካ ሁኔታ በመከናወኑ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን አብሮ ደስ አለን።
በቀጣይ የሀገራችንን የመልማት ፍላጎት ጥያቄን በሚመልስ መልኩ የጀመርነው ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ በሕዝባችን የነቃ ተሳትፎ እና ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ተፈጥሮ የሰጠችንን ታላቅ ጸጋ አልምተን ለመጠቀም በገንዘባችሁ፣ በጉልበታችሁ፣ በላባችሁና በዕውቀታችሁ ባደረጋችሁት ብርቱ ርብርብ ለዚህ ታሪካዊ ስኬት በመብቃታችን እንኳን ደስ አለን።
በዚህ የስኬት ግለት ሀገራችንን ለውጪ አካላት ተጋላጭ የሚያደርጉ ኃይሎችን በተባበረ ክንድ መመከትና ሴራቸውን ማምከን ይገባል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ታሪካዊ ፕሮጀክት በዚህ የስኬት ደረጃ ያደረሰ እንዲሁም በብዙ ጫናዎች ሳይበገር ሰላማዊ ምርጫ ያካሄደ ሕዝብ አንድነቱን አጥብቆና ጠብቆ ሲተም ለውጤት እንደሚበቃ ትልቅ ማሳያ መሆኑን መመልከት ይቻላል።
ኢትዮጵያን በየትኛውም አቅጣጫ የሚዳፈሩ እና የውጪ አካላት ፍላጎት አስፈፃሚ የሆኑ ሃይሎች ዳግም እንዳይመለሱ ሕዝቡ ተባብሮ ኃያልነቱን ማረጋገጥ አለበት።
ባለፉት ጊዜያት ከውስጥ እና ከውጭ በርካታ ኃይሎች የፈጠሩብንን ጫናዎች በጥበብ መሻገራችን አይዘነጋም፤ ወደፊትም ለሚጠብቁን ፈተናዎችም ሕዝቡ ሕብረቱን አጠናክሮ በንቃት መመከት ይጠበቅበታል።
ለዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ በመድረሳችን በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩ፤ በዘላቂነት አንድነታችንን አጠናክረን ትውልድ እና ሀገርን በድል እንድናሻግር ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
