ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን ሲያከብር በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳሰበ።

217

ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን ሲያከብር በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳሰበ።

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 12/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1 ሺህ 442ኛው የኢድል አል አድሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰይድ መሐመድ እንደገለጹት በእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የገንዘብ አቅም ያለዉ በእድሜ ዘመኑ አንድ ጊዜ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በመሄድ የሐጅ ሥነ ሥርዓት የሚከወንበት ነው፤ የኢድ ሶላት ከተጠናቀቀ ጀምሮ ደግሞ ከታረደዉ ሲሶ ለድሆዎች፣ ሲሶው ደግሞ ለቤተ ዘመድ እና ለጎረቤት እንዲሁም የተቀረው ሲሶው ለቤተሰቡ በመስጠት በጎ ተግባር የሚፈጸምበት ነው ብለዋል፤ ፕሬዝዳንቱ ሸህ ሰይድ መሐመድ።

ሼህ ሰይድ የሃይማኖቱ ተከታዮች በዓሉን በመፆም፣ ዱዓ በማድረግ እንዲሁም የኢድ ሶላት እና የእርድ ሥርዓት በመፈፀም ለተቸገሩት በማብላት እና ቤተሰባቸዉን በማስደሰት በዓሉን ማክበር እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

“በዓሉ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የነቢዩ ኢብራሂምን (ዐ.ሰ) ፈለግ በመከተል ለአላህ ፍፁም ታዛዥነትን ለማስታወስ የእርድ ሥነ-ሥርዓት ያከናወነ ነው፤ እኛም የነቢዩን ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሱና በመከተል ወደ አላህ በመቃረብ የምናደርገው የኢባዳ አካል ነው” ብለዋል ሸህ ሰይድ።

በመሆኑም ሕዝበ ሙስሊሙ በበዓሉ ቀን በጎ ተግባራትን በማከናወን የተቸገሩትንና የተራቡትን በመርዳት እንዲያከብር ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

በተለይም በክልሉ ብሎም በሀገር ደረጃ በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ወገኖችን መደገፍና ወደ ቀድሞዉ ሕይታቸዉና ቀያቸዉ በመመለስ ሁሉም የድርሻቸውን መወጣት ይገባዋል ነው ያሉት፡፡

ሸህ ሰይድ “የዚህ ዓመት በዓል ሲከበር ሀገራችን ሰላማዊ ምርጫ ያካሄደችበት፤ ከድህነት መዉጫ የረዥም ጊዜ የልማት ጥያቄያችን መፍቻ የሆነዉ የህዳሴ ግድባቸን የኹለተኛ ዙር የዉኃ ሙሌት የተከናወነበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በመገንዘብ ለሀገር አንድነት እና ሉዓላዊነት መከበር መሥራት እንደሚገባ ፕሬዝዳንቱ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ሸህ ሰይድ በመግለጫቸው እንዳሉት የዘንድሮው አረፋ በዓል ሲከበር ከመቸዉም ጊዜ በላይ ዱዓ እየተደረገ መሆን አለበት፡፡ ከቤተሰብ እና ከጎረቤት እንዲሁም ከሌሎች ሃይማኖት ተከታይ ወገኖች ጋር አብሮ በመብላትና በመደሰት ለዘመናት የዘለቀዉን የአብሮነትና የመተሳሰብ እሴት በማጎልበት ጭምር መሆን እንዳለበትም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።

ሸህ ሰይድ እንዳሉት የአረፋ በዓል መነሻ መሰረቱ ከነቢዩ አደም ጋር የተገናኘ ነው፤ “ነቢዩ አደም ከጀነት ከወጡ በኋላ ከእናታችን ሃዋ ጋር አረፋ ተራራ ተገናኝተው ‘አወቅከኝ፤ አወቅሽኝ’ የተባባሉበት ነው፤ ይኸዉ እስከ ዛሬም ድረስ ከመላው ዓለም የሚሰባሰቡ ሐጃጆች ብሔር፣ ጾታ፣ ቀለም፣ አህጉር፣ ሀገር ሳይገድባቸው አንድ አይነት የኢህራም ልብስ በመልበስ አረፋ በተባለ ልዩ ቦታ በአንድ ቦታ ቁመዉ ዱዓ ያደርጋሉ፤ ሁሉም የነቢዩ አደም ልጆች መሆናችዉን የሚያስመሰክሩበት ዕለት ነው” ብለዋል፡፡

ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበጣና ሐይቅ በተሰወረችው ጀልባ ህይወታቸው ያለፈ የሰባት ሰዎች አስከሬን ተገኘ።
Next articleየታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ተጠናቀቀ።