
በዘንድሮዉ ክረምት ሊከሰት የሚችለዉን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ እየሠሩ መሆናቸውን የብሔራዊ ሜትሮሎጅ ኤጀንሲ እና የአደጋ ስጋት እና መከላከል አመራር ኮሚሽን ገለጹ።
ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2013 ዓ.ም(አሚኮ) በዘንድሮዉ ክረምት ሊከሰት የሚችለዉን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ የቅድመ መከላከል ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸዉ ተመላክቷል። በሚቀጥሉት 10 ቀናት በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዝናብ መጠን እንደሚኖርም የብሔራዊ ሜትሮሎጅ ኤጀንሲ አስታውቋል።
የብሔራዊ ሜትሮሎጅ ኤጀንሲ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን እና የአደጋ ስጋት እና መከላከል አመራር ኮሚሽን በዘንድሮው ዓመት የሚኖረዉን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች ላይ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የብሔራዊ ሜትሮሎጅ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በሰሜን ምዕራብ አካባቢ ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን ሊኖር ይችላል ብለዋል።
ይህንን ተከትሎ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ተገቢዉን ቅድመ መከላከል ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። በተለይ በዓባይ ተፋሰስ እና በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ሊኖር እንደሚችል አስታዉቀዋል።
በዉኃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን አዳነች ያሬድ (ዶክተር ) ግቤ 1 እና ጣና በለስ ክረምቱ ከገባ ጀምሮ የዉኃ መጠናቸዉ እየጨመረ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
ቅድመ ጎርፍን ለመከላከልም የባለፈዉን ዓመት መነሻ በማድረግ የወንዝ ጠርዞችን የማስፋት፣ ደለል የማስወገድ እና ሰዉ ሰራሽ ወንዞችን የመፍጠር ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
በ7 ክልሎች በ5 ተፋሰሶች ላይ ወደ 600 ሚሊዮን ብር ተመድቦ የጎርፍ መከላከሉ ሥራ እየተሠራ መኾኑም ተነስቷል።
በአማራ ክልል በፎገራ ዓባይ ተፋሰስ አካባቢ የተጀመረዉ የጎርፍ መከላከል ሥራ ቀደም ብሎ 106 ሚሊዮን ብር ተመድቦለት እየተከናወነ መኾኑን ዶክተር አዳነች ጠቁመዋል።
የብሔራዊ የአደጋ ስጋት መከላከል ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መሲህ ዋሴ በብሔራዊ ሜትሮሎጅ የአየር ንብረት ቅድመ ትንበያ መሠረት የትኞቹ አካባባቢዎች በጎርፍ ይጠቃሉ የሚለዉን በመለየት የቅድመ ጎርፍ መከላከል ተግባራት እየተሠሩ መኾናቸዉን አንስተዋል።
ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የጎርፍ ተጋላጭ መሆናቸዉን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነር መሲህ ይህንን ለመከላከል በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ግብረ ኀይል ተቋቁማል ነዉ ያሉት።
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ጉኡሽ–ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
