
ለዘመቻ ህልውና ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ደጀንነታቸውን በተግባር እያሳዩ መሆናቸውን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለጹ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 12/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸባሪው ትህነግን ትንኮሳ ለመጨረሻ ጊዜ ለመግታት የሚደረገው የህልውና ዘመቻ መላውን ሕዝብ አሳትፏል፡፡ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም ለዘመቻ ህልውና ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ደጀንነታቸውን በተግባር እያሳዩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉ ሲሳይን ያገኘናቸው ግዳጅ ለሚገኙ የሚሊሻ አባላት ምሳ አዘጋጅተው እያበሉ ነበር። የዋግ ሕዝብ በየዕለቱ ለፈጣሪው የሚጸልየው “የምበላው አታሳጣኝ” ብሎ ሳይሆን “የማበላው አታሳጣኝ” ብሎ ነው ብለውናል ወይዘሮዋ።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች አሸባሪው ትህነግን ለመደምሰስ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ወይዘሮ ሙሉ ነግረውናል። “ለኛ መኖር ሲሉ ሕይወታቸውን ያለስስት ለሚሰጡን ልጆቻችንና ወንድሞቻችን ደጀን ሆነን ምንም ነገር ብናደርግላቸው አንረካም” ነው ያሉት ወይዘሮ ሙሉ፡፡
“የጦርነት ጥሩ ጎን ባይኖረውም ‘ልጨቁናችሁ’ የሚል ኃይልን አደብ ማስገዛት ስለሚያስፈልግ ጀግኖቻችንን አጀግን እንሸኛለን፣ ቢቆስሉ እናክማለን፣ ቢርባቸው እናበላለን፣ ቢጠማቸው እናጠጣለን፣ ለነሱ ሁሉንም ነገር እንሆንላቸዋለን” ብለዋል። በሀገር ህልውና ማስከበር ዘመቻው ላይ ለሚሳተፉት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ድጋፋቸው እስከ ድል አጥቢያ እንደሚቀጥል ነው ወይዘሮ ሙሉ የገለጹት።
ወይዘሮ ዝና ጌታቸው ለዘመቻ ሕልውና የሚደረገውን ድጋፍ እያስተባበሩ ነው ያገኘናቸው። የብሔረሰብ አስተዳደሩ ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ አርሶ አደሮች አቅሙ በፈቀደው ሁሉ ለህልውና አስከባሪ ዘማቾች ድጋፍ በማድረግ የኋላ ደጀንነቱን እያስመሰከረ ነው ብለውናል።
ወይዘሮ ዝና ነዋሪው ካለው ላይ ቀንሶ እና በጉልበት ጭምር በማገዝ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ አሻራውን እያሳረፈ ነው ብለዋል። የመንግሥት ሠራተኞች የወር ደሞዛቸውን ለዘመቻው እያዋጡ ሲሆን በብሔረሰብ አስተዳደሩ በአንድ ሳምንት ውስጥ በዓይነት የተሰበሰበው ሀብትም ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ነግረውናል።
የደም ልገሳ፣ የበጎ አድራጎት እና ሌሎችም ድጋፎች የሀገር ህልውና እስኪከበር ድረስ እንደሚቀጥሉም ነው ወይዘሮ ዝና ጌታቸው የገለጹልን። የምሳ ግብዣ ሲደረግላቸው ካገኘናቸው የሚሊሻ አባላት መካከል አቶ ወለላው አና እና አቶ ከፋለ ተሻገር የብሔረሰብ አስተዳደሩን ድጋፍ አወድሰው ድጋፉ ሁሉም ኢትጵያውያን የሀገራቸው ህልውና እንዲከበር መፈለጋቸውን ማሳያ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- እሱባለው ይርጋ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
