
“የሀገር መከላከያ ሠራዊት አሁን ላይ በሀገራዊ እይታና አንድነትን በሚያስጠብቅ ቅኝት ተደራጅቷል” ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የምትፈልገው የኢትዮጵያ የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን ወታደር ነው ሲሉ የሀገር መከላከያ የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ ገለጹ።
ከሦስትና አራት አመታት በፊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአቢዮታዊ ዲሞክራሲ የመጨረሻ ምሽግ እንጂ የኢትዮጵያ እንዳልነበረም ጠቁመዋል።
ሌተናል ጀነራሉ ይህን ያሉት ዛሬ አርትስ ቴሌቪዥን ባዘጋጀው “ጦቢያ” ፕሮግራም ላይ ነው።
ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቷ የመጨረሻ ምሽግ እንጂ የአንድ ፖለቲካ ድርጅት ምሽግ አይደለም።

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገሪቷ ሁለንተናዊ ለውጥ የሚተጉባት ወቅት ላይ መሆኑን አመላክተው ይህም በመሰረታዊ ሐሳብ በመስማማት መሆኑን ጠቁመዋል። የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫን እንደ ማሳያ በማንሳት።
በሀገሪቷ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከስልጣን ይልቅ ሀገርን በማስቀደማቸው ምንጊዜም ክብር አለን ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለዘመናት የነበረው ወታደራዊ አስተምህሮ ሀገሪቷን ከሚመሯት ጋር የተቆራኘ ስለመሆኑ ያነሱት ሌተናል ጀነራል ባጫ፤ ይህም ለመሪዎችና ለሐሳባቸው ታማኝ አገልጋይ ቢሆኑም ኢትዮጵያን ወራሪ ባጋጠማት ጊዜ ለህይወቱ ሳይሳሳ ማንኛውንም መስዋእትነት ከፍሎ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ጠብቆ መቆየቱን ተናግረዋል። ይህም ከንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ እስከ ኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ድረስ መቀጠሉን አስረድተዋል።
በንጉሥ ኃይለሥላሴም ኾነ በደርግ ዘመነ መንግሥት ምንም እንኳን ወታደሩ በመሪዎች ዕሳቤና ርዕዮት ቢመራም ለሀገር ሲባል ዋጋ ሲከፍል መቆየቱን ገልጸዋል።
ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ግን ለዘመናት ሀገርና ሕዝብ ሲጠብቅ የነበረውን ሕዝባዊ ሠራዊትን በመበተን ኢህአዴግ ድርጅታዊ መከላከያ ሠራዊት መፍጠሩን ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ የምትፈልገው የኢትዮጵያ ወታደር ነው” ብለዋል ሌተናል ጀነራል ባጫ፡፡ ከዓመታት በፊት የነበረው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አሁን ላይ በሀገራዊ እይታና አንድነትን በሚያስጠብቅ ቅኝት መደራጀቱን ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌን ጨምሮ የተለያዩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መኮንኖች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል። ኢዜአ እንደዘገበው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ