
አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለመደምሰስ የጸጥታ መዋቅሩ በአስተማማኝ አቋም ላይ እንደሚገኝ የሰሜን ጎንደር ዞን ሚሊሻ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ማይጠብሪ ላይ አሸባሪው ትህነግ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ ከአማራ ክልል ከተለያየ ወረዳ ሚሊሻዎች ወደ ግንባር ገብተዋል።
የጃናሞራ እና የደባርቅ ወረዳ ሚሊሻዎች እንደነገሩን የህልውና ዘመቻ ላይ ከሚገኙት ኀይሎች ጋር በመኾን አሸባሪውን ቡድን ለመቅበር በአስተማማኝ አቅም ላይ እንደሚገኙ ነግረውናል።
ከማዕከላዊ ጎንደር እና ከጎንደር ከተማ የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለዉ የገቡ ሚሊሻዎች በበኩላቸዉ የጥቅምት 24ቱን ወረራ ለመቀልበስ መሳተፍቸዉን እና ድል ማድረጋቸውን አስታዉሰዉ አሁንም አሸባሪውን ቡድን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር በሚደረገው ጥረት በግንባር መሰለፋቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ሚሊሻዎቹ ለአሸባሪው ቡድን የማያዳግም ትምህርት ለመስጠት መዘጋጀታቸዉን ገልጸዋል፡፡
በሰሜን ጎንደር ዞን ሚሊሻ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የትጥቅና ጦር መሳሪያ አስተዳደር ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ ዓለምነህ ዝናቡ የጸጥታ መዋቅሩ አሸባሪው የትህነግ ቡድንን ለመደምሰስ በአስተማማኝ አቋም ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በሰንቅና በትጥቅ አስተማማኝ አቅርቦት እንዳለ የገለጹት አቶ ዓለምነህ ኀብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ይርጉ ፍንታ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ