ወጣቶች ከ’ሀውጃኖ’ ምን ይማራሉ?

538
ወጣቶች ከ’ሀውጃኖ’ ምን ይማራሉ?
ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያን አፍርሶ “ታላቅ” የሚለውን የራሱን ሀገር ለመመሥረት በማኒፌስቶ ጭምር ቀርጾ እንደሚሠራ ከራሱ ሰዎች ጭምር ሲነገር ተሰምቷል። ባለፉት 27 ዓመታት ሀገሪቱን ሲያስተዳድር የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቦታ ከፋፍሏል፡፡ አሸባሪው ትህነግ የአማራን ሕዝብ በጠላትነት በመፈረጅ ግፍና በደል ፈጽሟል፡፡ ይህን የአሸባሪውን ትህነግ ድርጊት ከተቃወሙ መካከል ይርጋ አበበ ወይንም በትግል ስሙ ‘ሀውጃኖ’ ይገኝበታል።
በራያ አላማጣ እንደተወለደ የሚነገረው ‘ሀውጃኖ’ ደርግን ለመጣል በተደረገው ትግል በወቅቱ ኢትዮጵያዊነትን ተላብሶ በተመሠረተው ኢህዴን ገብቶ ይንቀሳቀስ ነበር። የኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልም ነበር። ይሁን እንጅ አሸባሪው የትህነግ ቡድን የሚያራምደውን ድብቅ ሴራ የተረዳው ‘ሀውጃኖ’ አጥብቆ መቃወም ጀመረ። ስለ እኩልነትም መሟገት ጀመረ። ይህ የ’ሀውጃኖ’ አካሄድ ያልተዋጠላቸው የትህነግ ሰዎች በዓይነ ቁራኛ ይከታተሉት ጀመር። ሊያሳምኑት ቢሞክሩም ‘ሀውጃኖ’ ግን ከእውነት መሸሸትን አልመረጠም። በዚህ አቋሙ ያልተደሰቱት የአሸባሪው ትህነግ አባላት ከኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴነትም እንዲታገድ አደረጉት። ከነበረው ከፍተኛ ወታደራዊ ኀላፊነትም ዝቅ እንዲል አደረጉት። ነገር ግን ትህነግ የያዘው አቋም በሀገር ህልውና ላይ አደጋ እንደኾነ የተረዳው ጀግና ሹመት እና ንዋይ ሳያማልለው፣ ዛቻና ማስፈራራት ሳያግደው ለእውነት ቆመ፤ የትህነግን ሴራም ማጋለጡን ቀጠለ።
አካሄዳቸው የጋራ የሆነች ታላቅ ሀገር ለመምራት እንደማያስችልም በተደጋጋሚ ነገራቸው። ስውሩን የትህነግ ሴራ አላነቃንቅ ያለውን ታጋይ የአሸባሪው የትህነግ አባላት አንድ ነገር ለማድረግ ወሰኑ። ያን የለመዱትን የጭካኔ በትር አሳርፈው ‘ሀውጃኖ’ን ለህልፈት ዳረጉት፡፡
እናቶች በቤታቸው የእሳትን ረመጥ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆይላቸው አዳፍነው ያስቀምጡታል። ለሥራ ሲፈልጉ በአመዱ ውስጥ ተዳፍኖ የተቀመጠውን ረመጥ አንድደው ይጠቀማሉ። እውነትም ልክ በአመድ ውስጥ ተዳፍና የተቀመጠች ረመጥ ማለት ናት። ውሸታሞች በበዙበት ጊዜ እና ቦታ ትቀበራለች። እስከ መስዋእትነትም ታደርሳለች። ይሁን እንጅ ለእውነት የቆሙ ሰዎችን ህይወት ብታሳጣም እውነትን ራሷን መግደል አይቻልምና ልክ እንደረመጧ አንድ ቀን አድማሷን በማስፋት ሐሰተኞችን በምትኳ ትቀብራለች። ትህነግም የኾነው ይህንኑ ነው።
በትረ ስልጣኑን ሲቆናጠጥ ለእውነት የቆሙ ሰዎችን በመግደል እውነትን የገደለ መሰለው። ሰዎቹ ህይወታቸው ቢያልፍም የተዳፈነው እውነት ግን ጊዜዋን ጠብቃ ከተቀበረችበት ፈንቅላ ወጣች። ገዳዮቹ ከነበሩበት በትረ ስልጣን ሲባረሩ አብዛኛዎቹም በእውነት ሰይፍ ተቀልተው ላይመለሱ መቃብር ወረዱ።
በራያ ቆቦ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ልክ እንደ ‘ሀውጃኖ’ ትውልዱ ለእውነት ትግል ማድረግንና የጸና አቋምን መያዝ ይገባል ብለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ባለፉት 27 ዓመት የዘራውን የጥላቻ መርዝ ማስወገድ እንደሚገባ ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት።
ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች ውስጥ በላይ አስማረ እንደገለጸው ትህነግ ባለፉት 27 ዓመት በራያ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ በደል ፈጽሟል። በቋንቋቸው እንዳይናገሩ አድርጓል፤ የማንነት ጥያቄ ያነሱትን ገድሏል፤ አሳድዷል፤ አፈናቅሏል። ይህንን የትህነግ ግፍ ታዲያ ዳግም ላለመቀበል ለመፋለም መዘጋጀቱንም ነግሮናል።
ሌላው ነዋሪ ወሰን አሌ ልክ እንደ ‘ሀውጃኖ’ በመከባበር እና በአብሮነት ላይ የተመሠረተ ሀገር ለመፍጠር እንደሚታገል ገልጿል።
ወጣቱ ትውልድም የ’ሀውጃኖን’ ጀግንነት በመከተል በህልውናው የመጣውን ጠላት መመከት እንደሚገባው ተናግሯል።
ዓለሙ ደሱ የተባሉ ሌላው ነዋሪ የአሁኑ ትውልድ የተደቀነበትን የህልውና አደጋ ሊቀለብስ እንደሚገባ ገልጸዋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሕዝቡ በአንድነት ከጸጥታ ኀይሉ ጎን ሊቆም ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ- ከራያ ቆቦ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኒውዮርክ እና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአጣዬና ከሚሴ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ 75 ሽህ ዶላር በላይ ድጋፍ አሰባሰቡ።
Next articleቤተ እስራኤላውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለመተከል እና አካባቢው ተፈናቃይ ወገኖች የምግብ እና አልባሳት ድጋፍ አደረጉ፡፡