
በጣና ሃይቅ ላይ 13 የሚደርሱ ሰዎችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረችን ጀልባ መሰወር ተከትሎ ፖሊስ ተሳፋሪዎችን ለማግኘት የተጠናከረ አሰሳ እያደረገ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ 13 የሚደርሱ ሰዎችን በመያዝ በጣና ሃይቅ ስትጓዝ የነበረች አነስተኛ ጀልባ መሰወሯን ተከትሎ ፖሊስ ተሳፋሪዎችን ለማግኘት የተጠናከረ ፍለጋ ላይ እንደሚገኝ ነው ገለጸው።
የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምክትል ኮማንደር ቸርነት አስማረ እንደገለጹት ጀልባዋ የተሰወረችው በወረዳው አዲሰጌ ድንጌ ተብሎ ከሚጠራ ቀበሌ መነሻዋን በማድረግ ወደ ጎርጎራ ጉዞ ከጀመረች በኋላ ነው።
ተጓዦቹ ሐምሌ 9/2013 ዓ.ም ሌሊት እስከ 15 ኩንታል የሚደርስ ድንች ጭነው ጉዞ መጀመራቸውን ፖሊስ ከቤተሰቦቻቸው ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ገልጿል።
ምክትል ኮማንደር ቸርነት እንደነገሩን ጀልባዋ ከመዳረሻዋ ከመድረሷ አስቀድሞ ሰምጣ አልያም በማዕበል ተወስዳ ሊሆን ይችላል በሚል ፍለጋው አሁንም መቀጠሉን እና እስካሁን ፍንጭ አለመገኘቱን ነግረውናል፡፡
ከመነሻው እስከ መዳረሻው ያለው የውኃ ላይ ጉዞ የ15 ኪሎ ሜትር ርቀት እንዳለው የነገሩን ምክትል ኮማንደር ቸርነት በፍለጋው የሚገኘውን አዲስ ነገር በቀጣይ እንደሚገለጽ ነው ያብራሩት።
ዘጋቢ፡- ምስጋናው ብርሃኔ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ