
በሀረሪ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሀረሪ ክልል ለታላቁ የህዳሴ ግድብ በአምስት ወር ከአስራ አራት ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ።
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በክልሉ ከጥር 27/2013 ዓ.ም ጀምሮ የነበረውን የአምስት ወራት ቆይታ አጠናቆ ለድሬዳዋ አስተዳደር አስረክቧል።
ዋንጫው በክልሉ ነበረው ቆይታ በከተማና በገጠር በሚገኙ ዘጠኙ ወረዳዎችና የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ለግድቡ ገቢ ከማሰባሰብ ባሻገር ስለ ግድቡ ለኅብረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሠራቱን ተመላክቷል።
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ርክክብ በተደረገበት ወቅት የሀረሪ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ሚስራ አብደላ እንዳሉት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከሕጻን አስከ አዋቂ በግድቡ ግንባታ ላይ አሻራውን ያኖረበትና ከተባበርን የማንችለው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው፡፡ በብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች መካከል አንድነትን ያጠናከረ የቀጣዩ ብልጽግናችን ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዋንጫው በሀረሪ ክልል በነበረው ቆይታ 14 ነጥብ 5ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የገለፁት ደግሞ የክልሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሄኖክ ሙሉነህ ናቸው።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በሀረሪ ክልል በነበረው ቆይታ ድጋፍ ላደረጉ ወረዳዎችና የተለያዩ ተቋማት እንዲሁም ባለሃብቶች ዋንጫና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል። ዋንጫው በክልሉ የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ወደ ድሬዳዋ አስተዳደር ተሸኝቷል፡፡
የሀረሪ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ሚስራ አብደላ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ዋንጫን ለድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አሕመድ መሐመድ ቡህና ለሌሎች የካቢኔ አባላት አስረክበዋል። ፋብኮ እንደዘገበው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ