ʺፍቅርን ከማያልቀው ቀይ ባሕር የጠጣ ፡ ኢትዮጵያ ጣና ዳር ከወንድሞቹ ጋር ሊጨዋወት መጣ”

950
ʺፍቅርን ከማያልቀው ቀይ ባሕር የጠጣ
ኢትዮጵያ ጣና ዳር ከወንድሞቹ ጋር ሊጨዋወት መጣ”
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ማን ይሄን ይገምታል፣ ማንስ ይሄን ያልማል፣ መራራቅ አልፎ መነፋፈቅ ይመጣል ብሎ ማንስ አስቧል፡፡ እንዳይገናኙ ሲሉ አደረግናቸው፣ ጊዜ ጀግናው አንድ አድርጎ አሳያቻው፡፡ ፍቅር ለዘመናት የተጠራቀመን ቂም ያጠፋል እንጂ፣ ቂም ፍቅርን አያጠፋም፡፡ ፍቅር ዘመን አይገደብለትም፣ ዘመን አይተመንለትም፣ ፍቅር ኃያል ነው፣ ከዙፋን ያስነሳል፣ በደስታ የስሜት ባሕር ውስጥ ያሰምጣል፡፡
የጨለማው ዘመን በፍቅር ይታለፋል፣ የጠበበው መንገድ በፍቅር ይሰፋል፣ በአንድነት ያስተቃቅፋል፣ እስራኤላውያንን ተከፍሎ ያሻገረው፣ የፈርዖንን ሠራዊት ተመልሶ የዋጠው ኃያሉ ባሕር፡፡ ማን እንደርሱ ጥበብ ተሰርቶበታል፣ ማንስ እንደርሱ ታምር ታይቶበታል፣ ማንስ እንደርሱ የበዛ ሕዝብ ተሻግሮበታል፣ ታዛዡ ባሕር ለጌታው ወዳጆች ከሁለት ተከፈለ፣ የጌታውንም ወዳጆች በቀኝና በግራ ቆሞ አሳለፈ፡፡ የጌታውን ወዳጆች ለመዋጥ የመጡ ጠላቶቻቸውንም እንደ ነበረበት ተመልሶ አስጨነቃቸው፣ አስጮሃቸው፣ ዋጣቸውም፡፡
ግብፃውያንም የፈርዖን ሰረገሎቹም ፈረሰኞቹም ሠራዊቱም ሁሉ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ ዳር በበኣልዛፎን ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ ሰፍረው አገኙአቸው። ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አነሡ፤ እነሆም ግብፃውያን በኋላቸው ገሥግስው ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ።
ሙሴም አላቻው እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፣ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። በትርህን አንሣ፣ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፣ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፣ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ።
ታላቁ ሙሴም የተባለውን አደረገ፡፡ በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፡፡ ባሕሩንም አደረቀው፣ ውኃውም ተከፈለ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። ግብፃውያንም የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። ሙሴም ከፈጣሪው እንደታዘዘው ዳግመኛ በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፡፡ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፡፡ ውኃውም ተመልሶ በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን ፈረሰኞችንም የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደነ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልቀረም እንዳለ መጽሐፍ።
ሙሴ ባሻገረበት፣ ጥበብና ፍቅር በታዬበት፣ በታላቁ ባሕር አጠገብ በተፈጠረችው ውብ ምድር የሚኖሩ ውብ ሕዝቦች አሉ፡፡ በፍቅር ማቀፍ በጽናት ማለፍ ይችላሉ፡፡ እስከ ሞት ይታመናሉ፣ በንጹህ ልብ ያምናሉ፡፡ እነርሱም ኤርትራውያን ናቸው፡፡ ባሕረ ኤርትራን ወይንም ቀይ ባሕርን ተሻግሮ የሚሄደውና የሚመጣው ጥበብ፣ ፍቅርና በረከት ሁሉ ከእነርሱ ዘንድ አለ፡፡ በጥበብ በተከፈለው ባሕር ውስጥ እስራኤላውያን እንዳለፉ ሁሉ በጥበብ በተሰራው የኤርትራውያን ልብ ውስጥም ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ በኢትዮጵያዊያን ውስጥም ኤርትራዊያን አሉ፡፡ የማይነጣጠል ወዳጅነት፣ ዘመናትን አልፎ የማይደበዝዝ አንድነት፣ ነገን የሚያሻግር አስታዋይነት የጋራቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን በቀይ ባሕር መዋኘት፣ በአስመራ ጎዳናዎች መዝናናት፣ በምጽዋ ከወንድሞቻቸው ጋር መገናኘት ይመኙ ነበር፡፡ ኤርትራዊያንም ጽዮንን ማዬት፣ ነጃሽን መመልከት፣ ላልይበላ መገኘት፣ ጎንደር ላይ መደሰት፣ በጣና መዝናናት፣ አዲስ አበባ ጅማ፣ ድሬ፣ ሐረር፣ ሀዋሳ ያለ ገደብ መከተም ይመኙ ነበር፡፡ ታዲያ ክፉ ዘመን ገጠማቸውና ወንድማማቾችን አጣልቶ፣ መገናኛቸውን ዘጋግቶ ለዓመታት በናፍቆትና በስስት በአሻገር ሲያስተያያቸው ኖረ፡፡
ፍቅርራቸውና አንድነታቸው ያልገባቸውም እነዚህ ዳግም የመገናኘት ነገራቸው አበቃለት፣ የፍቅር ዘመን ተፈጸመ፤ ጥላቻቸውንም የሚፈታው አልተገኘም አሏቸው፡፡ እነርሱ ግን የፍቅር አምላክ የፍቅር ዘመን እንደሚያመጣላቸው በልባቸው ያስቡ ነበርና ጠላት ያላቸው ሳይሆን ፈጣሪ ያለላቸው ዘመን ደረሰ፡፡ በመካከለቻው የተዘጋባቸው አጥር ፈረሰ፣ ጨለማ ያጣለው ክፉው ዘመን ተገፈፈ፣ የናፍቆትና የብሶት ዘመን አለፈ፡፡ የልብ አምላክ የልባቸውን ሰጣቸው፡፡
እስራኤላዊያን ቀይ ባሕርን መሻገር አይቻለንም ሲሉ የጥበብ አምላክ በጥበበኛ ልጁ አድሮ አሻገራቸው፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራም አይገናኙም ሲሏቸው መልካም ዘመን መጥቶ አንድ አደረጋቸው፡፡ ክፉውን ዘመን አሳለፋቸው፡፡ ዓለማት ተገረሙ፡፡ ይህ እንደምን ይሆናል፣ እንደምንስ ይፈጠራል፣ እውን ፍቅራቸው ተመለሰ ወይ? አሉ፡፡ በፍቅራቸው የሚደሰቱት አብረዋቸው ተደሰቱ፣ በጥላቸው የሚያተርፉት ግን ተኮረፉ፡፡ ዳግም ሲገናኙ በፍቅር እንባ ተላቀሱ፣ ከልባቸው የኖረውን ፍቅር ዳግም አነገሱ፣ በአንድነት ታደሱ፡፡
የፍቅር ጊዜም ጨመረ፡፡ የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት የእግር ኳስ ውድድር ሊካሄድ ቀኑ ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያም አዘጋጅታቸዋለች፡፡ እንግዶቿንም በክብር ተቀብላለች፡፡ በክብርም እያስተናገደች ነው፡፡ በዚህ ውድድር ከሚሳተፉት ሀገራት አንደኛዋ ወዳጅ ሀገር ኤርትራ ናት፡፡ ኤርትራውያንም በውቧ ከተማ ባሕርዳር ከከተሙ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ በዚሕ ውድድር ከዓመታት በኋላ የኤርትራ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፣ ብዙዎችን አስደሰተ፡፡
ʺፍቅርን ከማያልቀው ቀይ ባሕር የጠጣ
ኢትዮጵያ ጣና ዳር ከወንድሞቹ ጋር ሊጨዋወት መጣ” ሌላ ደስታም መጣ፡፡ ቀይ ባሕር ዋኝቶ ያደገው፣ ከፍቅር ባሕር የጠጣው፣ በአስመራ፣ በምጽዋ፣ በከረን ጎዳናዎች ያደገው በፍቅር የተንሸራሸረው የኤርትራ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ከወንድሞቹ ጋር ይጫወት ዘንድ ሌላ እድል ተገኘ፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራ በአንድ ቡድን ተደለደሉ፡፡ የእነርሱን ጨዋታ ሜዳ ላይ ለማዬት ሰው ጓጓ፡፡ ቀኑም ደርሷል፡፡ ከቀይ ባሕር እስከ ባሕር ዳር ሀገሩ በፍቅር እረስርሷል፡፡ ፍቅር በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ ነግሷል፡፡ መልካም ዘመን ያመጣው መልካም ፍቅር፣ ሁሌም፣ ሁሉም ሊያዩት የሚመኙት ውብ ጨዋታ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየአሸባሪውን ትህነግ የመጨረሻ አስትንፋስ ለማቋረጥ ሁሉም በጋራ እንዲቆም የአፋር ክልል መንግሥት ጥሪ አቀረበ፡፡
Next articleየደብረብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።