
የአሸባሪውን ትህነግ የመጨረሻ አስትንፋስ ለማቋረጥ ሁሉም በጋራ እንዲቆም የአፋር ክልል መንግሥት ጥሪ አቀረበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሽብር ቡድኑ በአፋር ሕዝብ ላይ ጦርነት መክፈቱን አስታውቋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ አድማሱን ወደ አፋር ክልል በማስፋት የአፋር አርብቶ አደር ሕዝብ ላይ ጦርነት መክፈቱን የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።
ይህ እኩይ ቡድን በዳር ድንበር አስከባሪው፣ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው ጀግናው የአፋር አርብቶ አደር ሕዝብ ላይ በፈንቲ ረሱ ዞን ያሎ ወረዳ በኩል የከፈተውን ጦርነት መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ይመክታል ብሏል።
ሰላማዊ ክልላችንን ለማተራመስ ሽብርተኛው ትህነግ የለኮሰውን ጦርነት በአጭሩ እንዲገታ አርብቶ አደር ሕዝብ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ የሚጠበቅ እንደሆነ እና አካባቢውንም በንቃት ሊጠብቅ እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።
የክልሉ ሚሊሻ እና አጠቃላይ የፀጥታ ኃይሉ ይህን በሕዝብ ላይ የተሠነዘረውን ጥቃት የመከላከል ሥራ በቁርጠኝነት የሚተገብር ይሆናል ብሏል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም እንደ አበደ ውሻ እዚያና እዚህ ለመንከስ የእብደት ሥራ እየሠራ ያለውን ይህን እኩይ ቡድን በፍጥነት ግብአተ መሬቱ እንዲፈፀም እንደወትሮው ሁሉ እጅ ለእጅ በመያያዝ በጋራ በመታገል እስትንፋሱ እንዲቋረጥ ማድረግ ይጠበቅብናል ብሏል።
ሕዝቡም ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም ሽብርተኛው ቡድን በፈንቲ ረሱ ያሎ ወረዳ በኩል የተከፈተውን ጦርነት እንዲመክት ጥሪ አቅርቧል፡፡ ሕዝቡ በንቃት አካባቢውን በመቃኘት ከአካባቢው የፀጥታ ኃይል ጋር በትብብር እንዲሠራ ጥሪ ቀርቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ