በሥነ ምግባር የታነጹ፣ በእውቀት የዳበሩ እና በሃሳብ ልዕልና የሚያምኑ ተማሪዎችን ለማፍራት እየሠራ መሆኑን የወልድያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

93
በሥነ ምግባር የታነጹ፣ በእውቀት የዳበሩ እና በሃሳብ ልዕልና የሚያምኑ ተማሪዎችን ለማፍራት እየሠራ መሆኑን የወልድያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያስለጠናቸውን ተማሪዎች ለስምንተኛ ዙር እያስመረቀ ነው፡፡
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀው “ኽርት ኮንቬንሽን 2021” የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የላቀ አፈፃፀም በማስመዝገብ የሜዳሊያ፣ የዋንጫ እና የእውቅና ባለቤት መሆኑን የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አበበ ግርማ (ዶክተር) ገልጸዋል፡፡
ይህ ድል በተመዘገበበት ማግስት የሚከበር የተማሪዎች የምረቃ ሥነ ስርዓት በመሆኑ ምረቃችሁን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ ለተመራቂ ተማሪዎች፡፡
ትምህርት ለአንድ ሀገር እድገት ቁልፍ መሳሪያ ነው ያሉት የዩኒቨርቲው ፕሬዚዳንት በሥነ ምግባር የታነጹ፣ በእውቀት የዳበሩ፣ በተግባር የተፈተኑ እና በሃሳብ ልዕልና የሚያምኑ ተማሪዎችን ለማፍራት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር አበበ ዩኒቨርሲቲው በ10 ዓመታት የሥራ ዘመኑ 11 ሺህ 882 ባለሙያዎችን በማሰልጠን ወደ ሥራው ዓለም ማሰማራቱን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ እያስመረቃቸው የሚገኙት የ2013 ዓ.ም ተመራቂዎች 2 ሺህ 537 የስምንተኛ ዙር ተመራቂዎች ናቸው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያ እና ኹለተኛ ዲግሪ የትምህርት መስኮች ከ21 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ እና በመደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች እያሰለጠነ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ በዘለለ በጥናት እና ምርምር ሥራዎች በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ዶክተር አበበ አብራርተዋል፡፡ ከውጭ የምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወሎ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በሚገኙ 10 ወረዳዎች ከ30 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የምርምር ሥራዎችን እያከነዋነ ነው ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በአካባቢው ተከስቶ የነበረውን የበርሃ አምበጣ ለመከላከል በርካታ ሥራዎችን እንደሠራ ተናግረዋል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ዩኒቨርሲቲው ካከናወናቸው ተግባራት በተጨማሪ 20 ሺህ ናሙናዎችን በመመርመር ሀገራዊ ተልዕኮውን ተወጥቷል ተብሏል፡፡
ፕሬዚዳንቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የሕክምና ቁሳቁስ ለሆስፒታሎች ማበርከቱን ገልጸው የወልድያ ከተማ ንድፍ ሥራንም ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ በሚያወጣ ገንዘብ በመምህራኑ አሠርቶ ማስረከቡን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በወልድያ ከተማ የአይሲቲ ተቋም አቋቁሞ ከመስጠቱ በተጨማሪ ስልጠና፣ ለትምህርት ቤቶች ቁሳቁስ ድጋፍ፣ ባህልና ቱሪዝም እና ሌሎች መስኮች ላይ የሚጠበቅበትን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በመጨረሻም ተቋማቸው ችግር በገጠመው ወቅት ከጎናቸው በመቆም ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየመመረቂያ ውጤቱ ከምስክር ወረቀት ባለፈ በሕይወት የሚተገበር እንዲሆን መሥራት እንደሚገባ ተመላከተ፡፡
Next articleአሸባሪው ህወሓት የትግራይ ህጻናትን በሀሽሽ አዕምሯቸውን አደንዝዞ ወደ ጦርነት እየማገደ መሆኑን ዶክተር አረጋዊ በርሄ ገለጹ።