የመመረቂያ ውጤቱ ከምስክር ወረቀት ባለፈ በሕይወት የሚተገበር እንዲሆን መሥራት እንደሚገባ ተመላከተ፡፡

121
የመመረቂያ ውጤቱ ከምስክር ወረቀት ባለፈ በሕይወት የሚተገበር እንዲሆን መሥራት እንደሚገባ ተመላከተ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ወልድያ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል፡፡
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የወልድያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ሹሜ ደጉ ትምህርት የሕይወትና የተፈጥሮ ሚስጥር መክፈቻ ዋና ቁልፍና ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ልማት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ለሀገር ልማት መረጋገጥ የተማረ፣ የተመራመረ፣ ጥበብ ወይም የለማ አዕምሮና የሰለጠነ አስተሳሰብ ያለው የሰው ኃይል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ጥበብን ለዓለም የዘራች ናት ያሉት ኀላፊው በሌሎች ዓለም የማይገኙ ቅርሶችን የያዘች ሀገር ስለመሆኗም ተናግረዋል፡፡
አቶ ሹሜ ኢትዮጵያ በገጸ ምድር፣ በከርሰ ምድር ሀብትና በዓየር ንብረት የታደለች ሀገር ናትም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የሁሉም ሃይማኖቶች ጥንተ መሠረት የኾኑ ሃይማኖቶች መገኛ ሀገር ስለመሆኗም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት አንባ ሀገር ናት፤ ይሁን እንጂ ባለንበት ክፍለ ዘመን ከዓለም በፊት መሰለፍ ቀርቶ ከኋላ ቀርተን የዓለም እኩይ ድርጊቶችና ሸቀጦች ማራገፊያ ሆነናልም ብለዋል አቶ ሹሜ፡፡
ኢትዮጵያውያን አሁንም በበሬ የሚያርሱና አኗኗሩ ባልተቀየረ ገበሬ ትክሻ ተንጠልጥለው የሚኖሩ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል፤ ይህን ለመቀየር መሥራት እንደሚገባ በመጥቀስ፡፡
ጽሕፈት ቤት ኀላፊው ራስን ካለመለወጥ አልፎም በዘርና በቋንቋ በመከፋፈል ለማኅበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እየተጋለጥን ነው ብለዋል፡፡ ዜጎች በሀገራቸው የመኖር ዋስትና ተነፍጓቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን፣ ሀብትና ንብረት መውደሙን እና ለሕልፈት መዳረጋቸውንም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያንን ለብዙ ችግሮች የዳረጋቸው ስርዓት በተባበረ ክንድ ቢጥሉትም አሁንም ከፊት ለፊታቸው ያልጨረሷቸው ሥራዎች ስለመኖራቸው አቶ ሹሜ ገልጸዋል፡፡
አቶ ሹሜ መማርና መጠየቅ ጉዳዮችን በአመክንዮ መፈተሸና ለችግሮች መፍትሔ መፈለግ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ተመራቂ ተማሪዎች በተማሩበት መስክ ሀገር የገጠማትን ፈተና የሚያልፉበትና ያልተነካውን የኢትዮጵያን ሀብት የሚከፍቱበት ቁልፍ እንዲሆንም አሳስበዋል፡፡
የመመረቂያ ውጤቱ ከምስክር ወረቀት በላፈ በሕይዎት የሚተገበር እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡ የሕይዎት ምዕራፍ በርካታ እድሎች እንዳላት ሁሉ ፈተናዎች ስለመኖራቸውም ያመላከቱት ኀላፊው የተግባር መዕራፍ የሚጀመርበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተመራቂዎች ከፊት ለፊታቸው የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ተስፋ ባለመቁረጥ ፈተናዎችን በጥንካሬ በማለፍ ወደ እድል በመቀዬር ራስንና ሀገርን እንዲለውጡም አስገንዝበዋል፡፡
ጥላቻን ትተው ፍቅርን፣ መለያየትን ትተው መከባበርን እና አንድነትን፣ ተንኮል እና ሴራን ትተው ሰላምና አንድነትን በመምረጥ ሀገራቸውን ከፍ እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡ ኢትዮጵያ የጠፋባትን መፍቻ ቁልፍ ለማግኘት በፍቅርና በአንድነት ሆነው እንዲተጉም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከርና ፈጣሪን መፍራት ለሀገራችን ትልቁ መፍትሔ ነው” ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ
Next articleበሥነ ምግባር የታነጹ፣ በእውቀት የዳበሩ እና በሃሳብ ልዕልና የሚያምኑ ተማሪዎችን ለማፍራት እየሠራ መሆኑን የወልድያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡