የኢትዮጵያ ማህጸን ዛሬም ጀግኖች ማፍራቱን አላቆመም…

1602
የኢትዮጵያ ማህጸን ዛሬም ጀግኖች ማፍራቱን አላቆመም…
ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ‹‹ወርቅ በእሳት ይፈተናል›› እንዲሉ ጀግኖች የአማራ ልጆችም የአባቶቻቸውን ገድል በህልውና ማስከበር ዘመቻ ላይ እየደገሙት ይገኛሉ፡፡ሰሞኑን በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ሲንሸራሸር የነበረውን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዛታ ግንባር ከአሸባሪው ትህነግ ጋር ፊት ለፊት ጦርነት ገጥሞ 32 ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ይጠቀሙበት ከነበረው አምቡላንስ ጋር ማርኮ ለብሔረሰብ አስተዳደሩ የጸጥታ ዘርፍ ያስረከበውን የአማራ ጀግና ታሪክ በስፍራው ተገኝተን እንዲህ ከትበነዋል፡፡
ጌታወይ ዓለሙ ይባላል፡፡ አሁን ላይ የዛታ ወረዳ የሰላምና ሕዝብ ደኅንነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነው፡፡ይህ ጀግና ተወልዶ ያደገው በሰቆጣ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ‹‹ትህነግ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የአማራ ጠላት ሆኖ የተፈጠረ ድርጅት ነው››የሚለው ጌታወይ ይኼው አሸባሪ ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ከጀርባው መውጋቱን ሲሰማ ከፍተኛ እልህና ቁጭት እንዳደረበት ይናገራል፡፡
የሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ሊጀመር ባለበት ወቅት በዛታ ወረዳ ሀሙሲት በምትባል አከባቢ ኾኖ የአሸባሪውን ትህነግ ቡድን መግቢያና መውጫ በግሉ ሲከታተል የነበረው ጌታወይ ዘመቻው ሲጀመር ጥራሪ የሚባለውን ጫካና ትልቅ ወንዝ ጣና ብርጌድ ለሚባለው የአማራ ልዩ ኃይልና ለመከላከያ ሠራዊት መንገድ የመራው ይኼው ጀግና ነበር፡፡
የዛታ ወረዳ ነዋሪዎች አማራነታቸውን በአሸባሪው ትህነግ ተቀምተው በግድ ያለማንነታቸው ሌላ ማንነት እንዲጫናቸው ተደርጎ ሲኖሩ እንደነበር የጠቀሰው ጌታወይ በዛታ በተደረገው የሕግ ማስከበር ዘመቻ አማራነታቸውን ተነጥቀው የነበሩት ዜጎች በእልልታ እንደተቀበሏቸው ያስታውሳል፡፡ በኮረም፣ በራያ አላማጣ፣ ወልቃይትና ሌሎችም አካባቢ የሚኖረው አማራ በተመሳሳይ በደስታ እንደተቀበሏቸው በመግለጽ ጭምር፡፡
አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያውያንን እንደዜጋ የማይቆጥር በመሆኑና በአድሏዊ አሠራራቸውም ቢሆን ደስተኛ ባለመሆኑ ለአምስት ዓመታት በበርሃ በትግል አሳልፏል።
አሸባሪው ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን በደል በመቃወም ‹‹ዱር ቤቴ›› ብሎ የቆየው ጌታወይ አሸባሪው ትህነግ ለዓመታት ሲያሳድደው ቆይቷል። በኋላም ለእስር ዳርጎታል፡፡
ያ የእስር ቤትና የጨለማ ጊዜ ለጌታወይ የበራው ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ነው፡፡ የአማራ ክልል እና የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ለፌዴራል መንግሥት የኔ መታሰር አማራ ከመሆኔ ጋር ብቻ መሆኑን አስረድተው እንድፈታ ተደርጓል፡፡ ይሄንን ውለታ ለዋሉልኝ የክልሉ መሪዎች በአማራ ሕዝብ ስም ምስጋናዬ ይድረሳቸው ብሏል ጌታወይ፡፡
በቅርቡ የትህነግ አሸባሪ ቡድን ወደ ዛታ ወረዳ ለጠብ አጫሪነት መግባቱን የገለጸው ጌታወይ የክልሉ መንግሥት የአማራ ሕዝብ ህልውናውን እንዲያስከብር በሰጠው መመሪያ መሰረት አቶ ጌታወይም በዛታ ግንባር ተሰልፎ ከአሸባሪው ትህነግ ቡድን አባላት ላይ 32 ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችንና አምቡላንስ ለብሔረሰብ አስተዳደሩ አስረክቧል፡፡
‹‹የአማራ ማንነቱ መከበር አለበት›› የሚለው የዋጉ ጀግና እሱ ለአማራነቱ ሲል በከፈለው መስዋእትነት ልክ ሌላው አማራ መስዋእትነት እንዳይከፍል በማለት እስካሁን ከቤተሰቦቹ ጋር እንዳልተቀላቀለ ገልጾልናል፡፡ አሁንም በትግል ላይ ይገኛል።
‹‹የአማራ ወጣቶች ህልውናቸውን ለማስከበር ብቻም ሳይሆን የአባቶቻቸውን ገድል ለመድገም ወደ ኋላ አይሉም›› ያለው ጌታወይ የክልሉ መንግሥት ይሄንኑ የወጣቶች ፍላጎትና አቅም በአግባቡ እንዲጠቀምበትና እንዲመራ ጠይቋል፡፡
በአደንዛዥ ዕጽ እየተመሩ የእሳት እራት የሚሆኑት የትግራይ ልጆች የነ ጌታቸው ረዳ የፖለቲካ እስትንፋስ መሆናቸውን ማወቅ ይገባቸዋል ብሏል፡፡ ጦርነት የባሕል ስፖርታችን ነው ብሎ ሲመጻደቅ የነበረው አሸባሪው ቡድን የጦርነት ወዳጅ መሆኑን ለዓለም ሕዝብ ቢያስመሰክርም ጦርነቱ ከኢትዮጵያውያን ጋር ከሆነ ግን ማሸነፍ እንደማይችል ደጋግሞ አይቶታል ነው ያለው፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬም ሆነ ነገ እንደ ጌታወይ ያሉ ጀግኖችን የምትወልድ ማሕጸነ ለምለም በመሆኗ እንኳንስ ለትህነግ አይነቱ አሸባሪ ይቅርና ለሌላውም አትንበረከክም። ሁሌም ጠላቷን እንዳሸነፈች ትቀጥላለች፡፡
ዘጋቢ:- እሱባለው ይርጋ – ከዋግ ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 8ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
Next article“ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከርና ፈጣሪን መፍራት ለሀገራችን ትልቁ መፍትሔ ነው” ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ