“ክልሎች ልዩ ኀይሎቻቸውን እና ሚሊሻዎቻቸውን ቢያዘምቱ የሚገርም አይደለም” አምባሳደር ኽርማን ኮህን “በትግራይ ክልል ህጻናት ወደ ጦርነት መሰማራታቸውን ዓለም በጥብቅ ሊያወግዝ ይገባል” ፕሮፌሰር አን ፊዝ ጄራልድ

250
“ክልሎች ልዩ ኀይሎቻቸውን እና ሚሊሻዎቻቸውን ቢያዘምቱ የሚገርም አይደለም” አምባሳደር ኽርማን ኮህን
“በትግራይ ክልል ህጻናት ወደ ጦርነት መሰማራታቸውን ዓለም በጥብቅ ሊያወግዝ ይገባል” ፕሮፌሰር አን ፊዝ ጄራልድ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል መንግሥት ከሳምንት በፊት በሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ዋሻ ውስጥ የከረሙት የአሸባሪው ትህነግ አባላት ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ የአሸባሪው ቡድን አባላት ከዋሻ ከወጡ ማግስትም ኢትዮጵያን በቅርብ ቀን እናፈርሳለን ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ይህን ተከትሎም አሸባሪው ቡድን ካህናትን፣ አዛውንቶችን፣ እናቶችን እና ህጻናትን አስከትሎ በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጥቃት ጀምሯል፡፡ ክልሎች አሸባሪው የትህነግ ቡድን የአዛዦቹን ተልዕኮ ተቀብሎ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የህልውና ስጋት ከመሆኑ በፊት ልናስወግደው ይገባል በማለት ፊት ለፊት ተጋፍጦ የአሸባሪውን ሴራ የሚመክተውን የአማራ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ እየተቀላቀሉ ነው፡፡
አሸባሪውን ቡድን ለማስወገድ የክልሎችን የጸጥታ ሃይል መዝመት አስመልክቶ በትዊተር ገፃቸው መልዕክት ያስተላለፉት አሜሪካዊው አምባሳደር ኽርማን ኮህን “ህወሐት የቀድሞው የሀገሪቷ ገዥ የአሁኑ አማጺ” ሲሉ ገልጸውታል፡፡
አሸባሪው ትህነግ በሙስና የተዘፈቀ እና አምባገነን ነበር ያሉት አምባሳደሩ ይህን ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው ዘመቻ ክልሎች ልዩ ኃይላቸውን መላካቸው የሚያስገርም አይደለም ብለዋል፡፡ ምክንያት ያሉት ደግሞ አማጺ ሲሉ የገለጹት ቡድን ከ1983 ዓ.ም ጅምሮ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ስልጣን ላይ ሲቆይ በደል አድርሶባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ቀድሞ ከትህነግ ቡድን ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንደነበራቸው የሚታሙት አምባሳደር ኽርማን ኮህን እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ስሌት ከ1989 እስከ 1991 ለሦስት ዓመታት ያክል የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ኅላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ አምባሳደር ኽርማን አንድ ወቅት የአማራ ብሔርን አስመልክቶ ባስተላለፉት የተሳሳተ መረጃ ከፍተኛ ወቀሳ ከደረሰባቸው በኋላ ይቅርታ መጠየቃቸውም ይታወሳል።
በተመሳሳይ በእንግሊዝ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነት አማካሪ እና የባልሲሊ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አን ፊዝ ጄራልድ “በትግራይ ክልል ህጻናት ወደ ጦርነት መሰማራታቸውን ዓለም በጥብቅ ሊያወግዝ ይገባል” ብለዋል፡፡
ይህ የጦር ወንጀለኝነት ነው ያሉት ፕሮፌሰር አን ጄራልድ ጉዳዩን ከዩጋንዳው አማጺ የሎርድ ሪሲስታንት አርሚ መሪ ጆሴፍ ኮኒ ጋር አመሳስለውታል፡፡
ፕሮፌሰሯ በትዊተር ገጻቸው ጉዳዩን እያዩ ዝምታን ለመረጡት ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ሀገራት ባስተላለፉት መልዕክት “ዝምታው በመጭው ትውልድ ፊት ውርደት ይሆናል” ሲሉ ኮንነውታል፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአምኒስቲ ኢንትርናሽናል በአዲስ አበባ የትግራይ ተወላጆችን በተመለከተ መንግሥትን ለመወንጀል የተጠቀመበት ፎቶ የሀሰት መሆኑ ተጋለጠ።
Next articleሽብርተኛውን ትህነግ ለመደምሰስ ዝግጁ መሆናቸዉን የአዲአርቃይ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።