“በመሀላችን የተገኘውን ደዌ የማጥፋትና ሀገራችንን ሰላሟን የመመለስ ኃላፊነታችን እንወጣ” የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

130
  1. “በመሀላችን የተገኘውን ደዌ የማጥፋትና ሀገራችንን ሰላሟን የመመለስ ኃላፊነታችን እንወጣ” የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም በሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ ፈፅሞ የማይደራደረው ሕዝባችን እንደ ወትሮው ሁሉ ከአያት ቅደመ አያት የተረከብነውን አደራ በአግባቡ በመወጣት ይህ በመሀላችን የተገኘውን ደዌ የማጥፋትና ሀገራችንን ሰላሟን የመመለስ ኃላፊነታችን እንወጣ ብሏል።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት “እናት ኢትዮጵያን የማተራመስ የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች አጀንዳ በልጆቿ ጥረት ይከሽፋል” በሚል ርእስ ያወጣው ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊትና በሀገር ላይ በፈፀመው እጅግ ዘግናኝ እና አረመኔያዊ ክህደት ሳቢያ አደብ እንዲገዛ እና ሸሽቶ የቀበሮ ጉድጓድ እንዲገባ መደረጉ ይታወቃል።

ይህ ቡድን የቀበሮ ጉድጓዱም ሆኖ ዘወትር በሚታወቅበት የቅጥፈትና የውሸት ፕሮፖጋንዳ ሕዝብን የማሳሳት ከዚያም አልፎ ለዓለም ሕዝብ የውሸት ወሬ በመንዛት የነበረውን እንዳልነበረ፣ ያልነበረውን እንደነበረ የማድረግ የማወናበድ ዘመቻውን አጧጧፈው።

ለሕግ ማስከበርና ህልውና ዘመቻው የተሰማሩ የኢትዮጵያ ጀግኖች ለወንድም የትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ ለመስጠትና ወቅቱ የእርሻ ጊዜ በመሆኑ እርሻውን እንዲያርስ በሚል አርቆ አሳቢነት አካባቢውን ለቀው በመውጣት መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያውጅም ሁሌም ጸረ ሕዝብ የሆነው ይህ ቡድን ሕዝቡ የጥሞና ጊዜ እንዳያገኝ የተኩስ አቁም አዋጁን በመጣስ ዳግም ጦርነት ከፍቷል።

ይህ አረመኔ ቡድን አረመኔያዊነቱን ይበልጥ ለማሳየት ገና ጨዋታ ያልጠገቡ የትግራይ እናት ልጆች ሕጻናትን በማሰማራት ለውጊያ አሰለፈ።

ቡድኑ የሚከተለው የሴራ ፖለቲካ ይባሱን በማፋፋም ተዳክሞ ከወደቀበት አፈር ልሶ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ህልሙን ለማሳካት የሞት ሽረት ትግል ለማድረግ መፍጨርጨር ይዟል።

ይህ እኩይ ቡድን ከዚህ ያልተገባ አረመኔያዊ ተግባሩ እንዲታቀብና በሽታው እንዳይዛመትም ሥርዓት የማስያዝ ሥራ ወንድም ትግራይ ሕዝብን ጨምሮ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት ነው የሚሆነው።

እንደምናውቀው እናት ሀገር ኢትዮጵያ ከፈጣሪ በታች በውድ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ሉዓላዊነቷን አስከብራ ነው ዛሬ ላይ የደረሰችው። አሁንም ቢሆን እኚህ ለሀገር ፀር የሆኑ ሰላም ፈፅሞ ሊገባቸው ያልቻለ፣ ቅድሚያ ለሀገር ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ያቃታው እኩይ ቡድን በሚገባው ቋንቋ በማናገር እንደ መዥገር ከወንድም ትግራይ ሕዝብና አጠቃላይ ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ የመገላገል ሥራ ተጠናክሮ ሊሠራ ይገባል።

መንግሥታችን ሁሌም ቅድሚያ ለሰላም፣ ቅድሚያ ለልማት፣ ጦርነት አይበጀንም፣ ክላሽ ሳይሆን ዳቦ ነው የሚያስፈልገን ቢልም ይህ ቡድን አሻፈረኝ በማለት ይሄው ዛሬም ድረስ ያገኛትን መሿለኪያ ቀዳዳ በመጠቀም በሕዝብ ሉዓላዊነት ላይ ሴራ በመሸረብ፣ በይፋም “ኢትዮጵያን እንበታትናለን” ብለው በመፎከር፣ ከፉከራም አልፈው በአንዳንድ ቦታዎች ጥቃት በማድረስ ላይ ስለሚገኝ ይህ የጭካኔ ጥግ የደረሰ ሴራውን በጋራ ልንመክት ይገባል።

በሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ ፈፅሞ የማይደራደረው ሕዝባችን እንደ ወትሮው ሁሉ ከአያት ከቅደመ አያት የተረከብነውን አደራ በአግባቡ በመወጣት ይህ በመሀላችን የተገኘውን ደዌ የማጥፋትና ሀገራችንን ሰላሟን የመመለስ ኃላፊነታችን እንወጣ።

እናት ኢትዮጵያ ከፈጣሪ በታች በውድ ልጆቿ ጥረትና ትጋት ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ሐምሌ 09/ 2013
ሰመራ

Previous articleአሸባሪው ቡድን ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ ድረስ ሙያዊ እና ግለሰባዊ ግዳጆቻቸውን እንደሚውጡ የአሚኮ ሠራተኞች ገለጹ፡፡
Next articleዘመቻችን የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግሥት የማጽናት ተልዕኮ ነው” የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት