አሸባሪው ቡድን ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ ድረስ ሙያዊ እና ግለሰባዊ ግዳጆቻቸውን እንደሚውጡ የአሚኮ ሠራተኞች ገለጹ፡፡

152
አሸባሪው ቡድን ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ ድረስ ሙያዊ እና ግለሰባዊ ግዳጆቻቸውን እንደሚውጡ የአሚኮ ሠራተኞች ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ትናንት በራሳቸው ተነሳሽነት ለጸጥታ ኅይሉ ደም የለገሱት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ሠራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ባደረጉት ስብሰባ ደግሞ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለሕልውና ዘመቻው ለግሰዋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በአማራ ልዩ ኃይል ላይ ጥቃት ሲፈጽም ፈጥኖ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለሕዝቡ በማድረስ ቀዳሚው ነበር ያሉት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ አስቻለ ዓየሁዓለም ኮርፖሬሽኑ ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የመረጃ ምንጭ በመሆንም ማገልገሉን ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ በሁሉም ግንባሮች ጋዜጠኞችን በማሰማራት ለሕዝቡ የነበረውን እውነት ገልጧል ያሉት አቶ አስቻለው ምንአልባትም የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን በስፍራው ቀድሞ ባይደርስ ኖሮ የማይካድራ ጭፍጨፋ ለዓለም ጆሮ ባለደረሰ ነበር ይላሉ፡፡
ተቋሙ እንደተቋም ለሕዝብ፣ ለሙያ መርህ እና ለፍትሕ መቆሙ የሚጠበቅ ነው፤ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞችም ሀገሩን እንደሚወድ ዜጋ ሁሉ አርዓያነታቸውን ደግመው ደጋግመው አሳይተዋል ይላሉ፡፡ ደም ልገሳን ጨምሮ በሕልውና ዘመቻው ለሚሳተፉ አካላት ዛሬ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለግሰዋል ነው ያሉት አቶ አስቻለው፡፡
የሕልውና ዘመቻው በስኬት እስከሚጠናቀቅም የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች እንደግለሰብ ኅላፊነታቸውን ይወጣሉ ብለዋል፡፡
በተቋሙ ለረጅም ጊዜ በጋዜጠኝነት ሙያ እያገለገሉ የሚገኙት እና በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ወደ ግንባር በመሄድ መረጃ ካደረሱ መካከል አንዱ ናቸው ጋዜጠኛ ምንይችል እንግዳ፡፡
የአሸባሪውን ትህነግ ድብቅ ሴራ ሙያዊ መርህን መሰረት አድርጎ ያጋለጠ እና ድምፅ የሆነ የብዙኃን መገናኛ ተቋም በመሆኑ አሸባሪው ቡድን አጥብቆ ይጠላው ነበር የሚሉት ጋዜጠኛ ምንይችል ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ሚዲያዎች እና ለዓለም ማኅበረሰብ የመረጃ ምንጭ በመሆን እያገለገለ ነው ይላሉ፡፡
በሕግ ማስከበር እርምጃው ከመከላከያ ሠራዊት እና ከአማራ ልዩ ኃይል ጋር በየአውደውጊያዎቹ በመገኘት ቀዳሚ መረጃ እንዳደረሰው ሁሉ አሁን ላይ በሕልውና ዘመቻውም ከየትኛውም የሀገር ውስጥ እና የውጭ የሚዲያ ተቋማት ቀድሞ ተሰማርቷል ነው ያሉት ጋዜጠኛ ምንይችል፡፡
ሀገራዊ ኃላፊነታችን በሙያችን ብቻ ሳይሆን በግለሰባዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ ስለሚገባ የአንድ ወር ደመወዝ ድጋፍ ለማድረግ መወሰናችን ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ በቀጣይም ለሀገራችን የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
ጋዜጠኛ የቻለ መልሰው በሕግ ማስከበር እርምጃው በወልቃይት እና አካባቢው አምርቶ እንደነበር ገልፆ ለህልውና ዘመቻው የአንድ ወር ደመወዝ መለገሱን ተናግሯል፡፡ በርካቶች በማንነታቸው ተሰድደዋል፣ ሕይዎታቸውን አጥተዋል፣ የአካል እና ሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል የሚለው ጋዜጠኛ የቻለ ይህንን የኢትዮጵያዊያን ሁሉ የህልውና ስጋት የሆነ ቡድን ለማስወገድ በሚደረገው ዘመቻ ሙያዊ እና ግለሰባዊ ግዴታችን ለመወጣት ዝግጁ ነን ብሏል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ሠራተኛ ወይዘሮ አስረስ ፈንታ ዛሬ ሠራተኛው የወሰነው የአንድ ወር ደመወዝ ለሌላው የኅብረተሰብ ክፍል አርዓያ እንደሚሆን ጠቅሰው በቀጣይም እስከ ሕይዎት መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
በመላው ኢትዮጵያዊያን የተጋረጠው የሕልውና አደጋ እስኪቀለበስ ድረስም በማንኛውም መንገድ ድጋፍ ለማድረግ እና ማኅበረሰቡን ለማንቃት እንተጋለን ነው ያሉት ሠራተኞቹ፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየሶማሌ ክልል አሸባሪው ህወሃትን እስከመጨረሻው ለማስወገድ የአማራ ክልላዊ መንግሥትና የፌደራል መንግሥት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፍ አስታወቀ።
Next article“በመሀላችን የተገኘውን ደዌ የማጥፋትና ሀገራችንን ሰላሟን የመመለስ ኃላፊነታችን እንወጣ” የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት