
ባሕር ዳር፡ መስከረም 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ባለፋት ሁለት ወራት ከ550 በላይ ኮንቴነር መድኃኒቶችንና የሕክምና መገልገያ ግብዓቶችን ከሞጆ ደረቅ ወደብ ማንሣቱን የኤጀንሲው የመድኃኒት ኮንትራት አስተዳደር ባለሙያ ወይዘሮ አጋር ተስፋዬ አስታወቁ፡፡
መድኃኒቶቹ ለኤች.አይ.ቪ፣ ለሆድ ሕመም፣ ለኢንፌክሽን፣ ለሥነተዋልዶ እና ለሌሎች አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶች፣ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችና ሪኤጀንቶች እንደሆኑ ወይዘሮ አጋር አብራርተዋል፡፡
ወይዘሮ አጋር ከ25 ዓይነት በላይ መድኃኒቶችን ከሞጆ ደረቅ ወደብ በማውጣት በተለያዩ ቅርንጫፎችና በዋናው መሥሪያ ቤት የመድኃኒት ማከማቻ መጋዘን እንደገቡ አስረድተዋል፡፡
መድኃኒቶቹንና የሕክምና መገልገያዎቹን ከሞጆ ደረቅ ወደብ ወደ ተለያዩ ቅርንጫፎች በቀጥታ ማሠራጨታቸውንና ወደ ቅርንጫፍ ቀጥታ መሄዱም ጊዜንና ወጪን በመቆጠብ ለማኅበረሰቡ በቶሎ መድኃኒቶችን ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ ሚና አለው ሲሉ ባለሙያዋ አክለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከባንክ የኦርጅናል ዶክመንት መዘግየት ጋር በተያያዘ ከሞጆ ደረቅ ወደብ መድኃኒቶችን በወቅቱ ለማንሣት እክል ይገጥም እንደነበርና ይህንንም ለመፍታት ኤጀንሲውና ባለድርሻ አካላቱ ተወያይተው ችግሮቹን በመፍታት መድኃኒቶቹ እንደገቡ ባለሙያዋ አብራርተዋል፡፡
በቀጣይም መሠል እክሎች እንዳይከሠቱ በባንኩ፣ በሞጆ ደረቅ ወደብ፣ በኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እና በኤጀንሲው መካከል ውል ለመፈራረም በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ባለሙያዋ ገልፀዋል፡፡
ውሉም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለኤጀንሲው ተልዕኮ ቅድሚያ በመስጠት ሥራዎችን ለማሣለጥ ሰፊ ውይይት ከኤጀንሲው ጋር መካሄዱን አስረድተዋል፡፡
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ማኅበራዊ ገጽ