ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ ኀልውና በአርበኝነት መንፈስ እንዲነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ጥሪ አቀረበ፡፡

231
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ ኀልውና በአርበኝነት መንፈስ እንዲነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ጥሪ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከምሥረታው ጀምሮ ኢትዮጵያን በመበታተን በኢትዮጵያ ፍርስራሸ ላይ ታላቋን የትግራይ ሪፐብሊክ መመሥረትን አቅዶ የተነሳው ትህነግ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ከኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ደመኛ ጠላቶች የመሳሪያ፣ የገንዘብ፣ የቁስ፣ የፖለቲካ እና የሞራል ድጋፍ በመጨረሻም ምዕራብ እና ምሥራቅ በሚል ሲካሄድ የነበረው የርዕዮተ ዓለም ጦርነት በአሜሪካ አሸናፊነት መቋጨቱን ተከትሎ ውግንናዉ ሶቪዬት ሕብረት ከምትመራው የምሥራቅ ወገን የነበረው የደርግ መንግሥት ፈራርሶ ትህነግ በኢትዮጵያ ጠላቶች ትክሻ ታዝሎ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ገባ።
አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት በገባ ማግሥት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት በማፈራረስ ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ ገነጠለ፤ ከማንም በፊት የኤርትራን ሉዓላዊ ሀገርነት እወቁልኝ የሚል ማመልከቻ በመያዝ የተባበሩት መንግሥታትን በር አንኳኳ።
በርሃ የገባበትን ኢትዮጵያን በዘላቂነት የማፈራረስ ተንኮል እና ሴራ ለማሳካት ሕገ መንግሥት በሚል ሽፋን አፓርታይዳዊ የሆነ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲውን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከመጫን አልፎ የኢትዮጵያ ልጆች በጋራ በመቆም የፍትኀ እና የልማት ትግል እንዳያደርጉ “የጨቋኝ-ተጨቋኝ” ድርሰት በመድረስ የኢትዮጵያ ልጆች በጋራ ተባብረው ከመቆም ይልቅ ተነጣጥለው በመታገል በጨቋኙ የትህነግ መዳፍ እንዲወድቁ አደረገ። ትህነግ የወጣበትን የትግራይ ማኀበረሰብ ጨምሮ ኢትዮጵያን የማፍረሰ እና የኢትዮጵያን ልጆች እርሰ በርስ የማፋጀት ተግባር የተቃወሙ እና የታገሉ ሀገር ወዳድ ዜጎችን ዘር፣ ጎሳ እና ብሔር ሳይለይ ጨፍጭፏል፤ አሰድዷል፤ በማሰቃያ ጣቢያዎች ውስጥ በማጎር ጤናቸውን በማቃወስ ልጆች ያለአሳዳጊ፣ ወላጆች ያለጧሪ እንዲቀሩ በማድረግ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ማኀበራዊ ምስቅልቀል እንዲደርስ ከማድረግ ጎን ለጎን የሀገሪቱን አንጡራ ሃብት የማፍያውን ቡድን ሥልጣን ላይ ለማቆየት እና የቡድኑን አባላት የቅንጦት ፍላጎት ለማሟላት በማዋል ኢትዮጵያን ራቁቷን አስቀርቷታል።
ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን ለመምራት አራት ኪሎ ገብቶ ሲያበቃ ከበርሃ ይዞት የመጣውን የነጻ አውጭነት ሥያሜውን ለመቀየር እንኳን ፍላጎት የሌለው ደርጅት የሚጠላትን ሀገር ከማፍረስ ተግባሩ እንዲቆጠብ ማድረግ የሚቻለው ትህነግን አዝለው አራት ኪሎ ካስገቡት የኢትዮጵያ ጠላቶች ፊት ሕጋዊነትን እንዲያገኝ በሚረዳው የይሥሙላ ምርጫ በመሳተፍ ሳይሆን በትጥቅ ትግል ነው የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረስ በ1993 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርን መሥርተን ታግለን አታግለናል፤ በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ታሪክ ሲዘከር የሚኖር አንጸባራቂ መስዋእትነት ከፍለን አልፈናል።
ኢትዮጵያዊያን ለዓመታት በተናጠል ዋጋ የከፈሉለት የነጻነት፣ የፍትኀ፣ የዕኩልነት እና የብልጽግና ጥያቄ ትህነግ ያቆመውን የልዩነት ግንብ ደርምሰው በአንድነት ቆመው በመታገላቸው በድርጅቱ ውስጥ የለውጥ ኀይሎች እንዲፈጠሩ በማድረግ የትህነግ ፍጽም ፈላጭ ቆራጭነት እንዲያከትም አደረገ።
ከጅምሩ የበላይነትን እንጂ ዕኩልነትን ለመቀበል አንዳች ፍላጎት የሌለው የትህነግ ማፍያ ቡድን በሥልጣን ዘመኑ የፈጸመውን ግፍ እና ሰቆቃ በይቅርታ በማለፍ በጋራ ጠንካራ ሀገር እንገንባ በማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ያቀረበለትን ጥሪ ከመጤፍ ሳይቆጥር ከውስጥ ኢትዮጵያን እየቦረቦረ የውጭ ጠላቶቿን ጋብዞ ሲያበቃ ከጀርባው በመሆን በታሪክ ጥቁር መዝገብ ውሥጥ የሚሰፍር ጥቃት በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ፈጸመ። ይህንን ተከትሎም መንግሥት የወሰደው የሕግ ማሥከበር እርምጃ አኩሪ ገድል የተፈጸመበት ተጋድሎ ነበር፡፡
ዓለምአቀፋን የዲፕሎማሲ ጫና ለማርገብ እንዲሁም ለትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ ለመስጠት ብሎም አርሶ አደሩ ሕዝብ የግብርና ተግባሩን ያለምንም ጦርነት ሥጋት እንዲከውን በሚል ቀና መንፈስ የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ከትግራይ መልቀቁን እንደምቹ አጋጣሚ የተጠቀመው አሸባሪው የትህነግ ጁንታ አፈር ልሶ በመነሳት ኢትዮጵያን ለመበታተን በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ላይ ያወጀውን ጦርነት የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በፍጹም ያወግዛል፡፡
በመሆኑም በለውጡ ማግሥት መንግሥት ያቀረበልንን የሰላም እና የእርቅ ጥያቄ ተቀብላችሁ መሳሪያችሁን በመጣል በተለያየ የሥራያ ዘርፍ የተሰማራችሁ አርበኞች “ውርሳችን አርበኝነት ትርፋችን ታሪካዊነት ነው!” የሚለውን መፈክራችንን በመያዝ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን የትህነግ ጁንታን ከመግሥት ጎን ተሰልፋችሁ እንድትፋለሙ የከበረ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በመጨረሻም የቀደሙ አባቶቻችን በየዘመኑ ከተነሱ የውስጥ ባንዳዎች እና የውጭ ወራሪዎች ጋር ታላቅ የአርበኝነት ተጋድሎ በመፈጸም ያወረሱንን ውርስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገር ሲኖረን ብቻ ሊፈቱ የሚችሉ ልዩነቶችን ወደጎን በመተው ለኢትዮጵያ ኀልውና በአርበኝነት መንፈስ ይነሳ ዘንድ የከበረ ጥሪያችንን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እናቀርባለን!!
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር
ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም
ባሕር ዳር፡ ኢትዮጵያ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየገቢዎች ሚኒስቴር እና በስሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማት በአማራ እና በአፋር ክልል ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚውል 135 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አደረጉ።
Next articleየማይካድራ ከተማ ወጣቶች የአሸባሪው ትህነግ ቡድንን ለመደምሰስ ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ፡፡