
የገቢዎች ሚኒስቴር እና በስሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማት በአማራ እና በአፋር ክልል ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚውል 135 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አደረጉ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቀበታ ከዚህ በፊት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ የገቢዎች ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በጋራ በመሆን የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ የቆዩ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ ተቋማቱ ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን በሁሉም ዘርፍ እየተወጡ ነው፤ በዛሬው ዕለት የቀረበው ድጋፍም ከዚህ እውነት የሚመነጭ ነው ብለዋል። ከዚህ በፊትም ለሁለቱ ክልሎች ድጋፍ ማድረጋቸውንም አንስተዋል።
በሰሜንና ሰሜን ምዕራብ የአማራ ክልል አካባቢዎች እና በሰሜን አፋር ትግራይን በሚያዋስኑ የአፋር ክልል አካባቢዎች ሕግ የማስከበር የህልውና ዘመቻውን ተከትሎ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ግምታቸው ከ135 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የምግብና አልባሳት ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል።
የገቢዎች ሚኒስትሩ ላቀ አያሌው ሀገርን ለማፍረስ እየሠራ ያለውን አሸባሪውን ትህነግ ለመደምሰስ 24 ሰዓት ህይወቱን እየሰጠ ለሚገኘው ሠራዊት የበኩላችን ለማድረግ የተደረገ ድጋፍ ነው ብለዋል፡፡ ሕግ በማስከበር ሥራ ላይ ላለው ሠራዊት ድጋፉ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡ ዛሬም 135 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ድጋፍ ለሁለቱ ክልሎች ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ትግሉ የሚጠይቀውን በማድረግ ለሀገር ህልውና የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል። ትህነግ በኢትዮጽያ ሕዝብ ላይ ታሪክ የማይረሳው ብዙ ግፍ ፈጽሟል፤ ይህን የሀገር ሰንኮፍ ለማስወገድ በሚደረገው የህልውና ዘመቻ ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው አካላት ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
የውጭ አካላት መርጠው በማልቀስ የአሸባሪውን ትህነግ ወንጀል በመደበቅ እየሄዱበት ያለው መንገድ ትክክል ባለመሆኑ እውነታው ሲወጣ ያፍራሉ ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመሻገር መደጋገፍና መመከት ሁሉን አቀፍ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት። ጁንታውን ለመደምሰስ በሚሠራው ሥራ የውስጥ ባንዳን በትኩረት መከታተል እና በያሉበት መታገልና ማጥራት ኢትዮጵያ እንድትቀጥልና ሕዝቦቿ ሰላም እንዲሆኑ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
እኛን ለጠምዘዝ የሚሰሩ አካላትን ለመታገል ራስን መቻል ነው ያሉት ሚኒስትሩ ለዚህም ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ይገባል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ዜጋ ኀላፊነቱን ሊወጣና ባለቤት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ የቆመውን የጁንታውን ቡድን በማስወገድ ሀገርን እና ሕዝብን በሰላምና በልማት ለማስቀጠል ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል ሚኒስትሩ።

ደም በመለገስ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስና በሌሎችም ማኅበራዊ ሁነቶች ተቋማቱ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የህልውና ዘመቻውን በድል ለመወጣት ሀብት መሰብሰብ ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ እንደ ገቢዎች ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ሁሉ ሌሎችም ሊያግዙን ይገባል ብለዋል።
አንድ ላይ በመቆምና በመደጋገፍ ይህን የሀገር ሸክም ነቅሎ ለመጣል ሁሉም አለኝታነቱን በተግባር ሊያሳይ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፋንታሁን- ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ