
የትህነግ አሸባሪ ቡድን ሕጻናትን ለጦርነት በማሰለፍ እየፈፀመ ባለው ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆን ትዴፓ ጥሪ አቀረበ።
ባሕር ዳር: ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የትህነግ አሸባሪ ቡድን ሕጻናትን ለጦርነት በማሰለፍ እየፈፀመ ባለው ከባድ ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ጥሪ አቀረበ።
የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሻለ ንጉሤ እንደገለጹት ሕጻናትን ለጦርነት ማሰለፍ በኢትዮጵያም ይሁን በዓለም ሕግ በከባድ ወንጀል ያስጠይቃል።
የትህነግ አሸባሪ ቡድን ይህንን ሕግ በመተላለፍ ሕጻናትን በመመልመል ለጦርነት በማሰለፍ ወንጀል በመፈፀም ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ቡድኑ እየፈፀመ ባለው ከባድ ወንጀል ተጠያቂ ሊሆን ይገባል ብለዋል አቶ ተሻለ።
የትህነግ የጥፋት ቡድን የተለያዩ ወንጀሎችን የመፈፀምና ሀገር የማፍረስ ተልእኮ ይዞ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ያስታወሱት የትዴፓ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አሁን ላይ ደግሞ ሕጻናትን ወደ ጦርነት መማገዱን ተያይዞታል ብለዋል።
በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የትህነግ ቡድን በዓለም አቀፍ ሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የትግራይ ሕዝብም ምንም አይነት ዓላማና ምክንያት አልባ በሆነ ጦርነት ሕጻናት ልጆቹን ማጣት ስለሌለበት የቡድኑን እኩይ ድርጊት መቃወምና ማውገዝ አለባቸው ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት በተለይ የግብረሰናይ ድርጅቶች የሽብር ቡድኑ በሕጻናት ላይ የሚያደርሰውን ወንጀል እያዩ ዝምታን መምረጣቸው የሚያሳዝን ነው ብለዋል።
በአሸባሪ ቡድኑ ተግባር መላው ሕዝብ ጉዳት የሚደርስበት ቢሆንም በተለይ የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ በመሆኑ እንዲታገለው አቶ ተሻለ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ልጆችና ቤተሰቦቹን በውጭ ሀገራት እያኖረ የድሃ ልጆችን ወደ ጦርነት እየማገደ ያለውን የትህነግ ቡድን የትግራይ ሕዝብ ሊቀበለው አይገባም ነው ያሉት።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ የትህነግ የሽብር ቡድን በሕጻናት ላይ እየፈፀመ ያለውን ወንጀል በመቃወም በቅርቡ የአቋም መግለጫ እንደሚያወጣም አቶ ተሻለ ጠቁመዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መብት ኮንቬንሽን አንቀፅ 38 እንደተመለከተው ሕጻናት ለጦርነት ያለመመልመል፣ ያለመሳተፍ እና የመሳሰሉት መብቶች አሏቸው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ